ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆን ለዩኒቨርሲቲዎች ትልቅ ዕድል እንጂ ስጋት አለመሆኑ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ የኮሌጅ ዲኖች፣ ምክትል ዲኖችና የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እያደረገ ባለው የሽግግር ወቅት ተግባራት እና ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ በተደረገው ውይይት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆን ለዩኒቨርሲቲዎች ትልቅ ዕድል እንጂ እንደ ስጋት ሊወሰድ እንደማይገባው ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ ፕ/ር ፍቅሬ በሰጡት ማብራሪያ መድረኩ ቀደም ሲል የተጀመረው የለውጥ ስራዎች ላይ ያለውን የሀሳብ ግልጽነት የሚያስፈልጋቸው ሀሳቦች እንዲሁም በቀጣይነት የሚሰሩ ስራዎች ላይ ግልጽነት ለመፍጠር የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ጠቅሰው እንደ ሀገር የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች በቀጣዩ ሶስት ዓመታት ውስጥ ወደ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲነት እንዲገቡ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የሽግግር እቅድ አዘጋጅተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
አሁን እየተሰራ ያለው ሥራ አስመልክቶ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆን ለዩኒቨርሲቲው ምን የተለየ ጥቅም ይኖረዋል ከሚል ሀሳብ ጋር አያይዘው ራስ-ገዝነት ዩኒቨርሲቲያችንን የበለጠ የማብቃት፣ ራስን በራስ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የማስተዳደር እና በነጻነት የሚንቀሳቀስበት በአዋጅ በሚሰጠው ስልጣን እና የራሱ የሆነ የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት እንዲንቀሳቀስ የሚያስችለው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የበለጠ አቅም የሚያገኝበት ፣ የላቀ ስራዎችን እንዲሰራና ተልዕኮውንም በተሳካ ሁኔታ እንዲወጣ አቅምንና ዕድልን የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ፕ/ር ፍቅሬ አክለውም ራስ-ገዝነት ተቋማዊ ነጻነትና ስልጣን የሚሰጥ በመሆኑ አሁን ያለውን መዋቅር በራሱ ከልሶ በሚያዋጣው መልኩ የመቀየር እና የማሻሻል ብሎም ዩኒቨርሲቲውን የሚመሩ አካላትን እስከመሰየም የሚያችል አቅምንና ስልጣንን የመስጠት እንዲሁም የአካዳሚክ ነጻነትን በመስጠት ዩኒቨርሲቲው የራሱ የሆነ የተማሪዎች ምልመላና ቅበላ ፖሊሲ በማዘጋጀት በራሱ መስፈርት ተማሪዎችን የመቀበል መብት እና በየትምህርት ክፍሎች የሚኖሩ የተማሪዎች ቁጥር የመወሰን፣ የትምህርት ፕሮግራሞችንም ያለማንም ይሁንታና ጣልቃገብነት ተፈላጊነትንና ተመራጭነታቸውን በመመዘን በራሱ የመቅረጽ መብትና ስልጣን ብሎም የትምህርትና የስልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ የራስ የሆነ ማዕቀፍ እንዲኖር ነጻነትን የሚሰጥ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ራስ-ገዝነት በሚሰጠው የሰው ሀብትን የማስተዳደር ነጻነትንም ለዩኒቨርሲቲው የሚያስፈለገውን የሰው ኃይል ቅጥር፣ የደረጃ ዕድገትና የመሳሰሉትን በራስ መስፈርትን በመከተል ማከናወን የሚያስችል መብትን፣ በሚኖረው ፋይናንስ ነጻነትም የራስን ገቢ ማመንጨትና የመጠቀም መብትን የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህም ተቋሙ ዓላማውን ለማሳካት እስከአስቻለው ድረስ በተለያዩ የገቢ ማመንጫ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ገቢን በማመንጨት እና በራስ በመንቀሳቀስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመንግስት ጥገኝነት የሚላቀቅ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት እስከ 2018 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲው እስከ ሃያ በመቶ ድረስ በራሱ በጀት ለመጠቀም ግብ መቀመጡን ይንንም ለማሳካት በዩኒቨርሲቲው በጠቅላላው ሃያ የገቢ ማመንጫ ዘርፎች ተለይተው እየተሰራባቸው መሆኑን
ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ በራሱ ጥራት ያለው ትምህርና ስልጠና ለመስጠት፣ ያለን ሀብትን ያለብክነት በጥንቃቄ ለመጠቀም እና ተመራጭና ተወዳዳሪ የትምህርት ፕሮግራሞች እዲኖሩ ዕድል የሚሰጥ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በዋናነት ጠንካራ የሰው ኃይል ፣ ጠንካራ የሆነ የፋይናንስ አቅም እንዲሁም መሰረተ-ልማት መኖር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲውም ከ2016 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ እስካሁን የተደረገው ጥረት ሲያብራሩም የሰው ኃይሉን በተመለከተም በቂና ብቁ የሆነ የሰው ኃይል መኖር ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን አንዱና ወሳኝ ጉዳይ ከመሆኑ አንጻር በዚህ የሽግግር ወቅትም በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የአካዳሚክ ሰራተኞች ፕሮፋይል ማደረጀት ትልቅ ትኩረት የሚሰጠዉ መሆኑን አስታውሰው በዚህም ሰራተኛው ያለው የትምህርት ዝግጅት፣ ያካበተው ልምድ ፣ በምርምርና በህትመት ላይ ያለው ተሳትፎና አቅም ተመዝኖ ምን ያህል ብቁ እንደሆነ የሚመዘንበት አሰራር እየተተገበረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በውይይት መድረኩም አዲስ በተዘጋጀው የሰራተኞች ፕሮፋይል መሙያ ቅጽ ላይና በአጠቃላይ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተያያዙ ሀሳቦችንና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ፕ/ር ፍቅሬም ለተነሱት ሀሳቦችና ጥያቄዎች ዝርዝር ማብራርያን ሰጥተዋል፡፡ በማጠቃለያቸውም ላይ የዩኒቨርሲቲው ዕጣ ፋንታ በሰራተኞች እጅ ላይ ያለ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው በዚህ የሽግግር ወቅት በትጋት በመስራትና ራስን በማብቃት ብቁና ተወዳደሪ ሆኖ መገኘት እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ሰራተኛ በታላቅ የኃላፊነት ስሜት መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡