በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የነበረው የኢሲሰዩ የወደፊት አቅጣጫ ይፋ ሆነ
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (ኢሲሰዩ) የወደፊት አቅጣጫ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሪፎርም ጥናት ውጤት የኢሲሰዩ የወደፊት የአዲስ ምዕራፍ የለውጥ ጉዞ ማብሰሪያ በሚል በተዘጋጀው መርሀ-ግብር የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትርና የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በተገኙበት መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ ተደረገ፡፡
በሪፎርም ጥናት ውጤት ማብሰሪያ መድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በሰጡት አቅጣጫ ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምዱ፣ ብቃትን የተላበሱ እና ነጻና ገለልተኛ በመሆን፤ በጥሩ በሥነ ምግባር የታነጹ፣ በአጠቃላይ ለሁኔታዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚችሉ፣ ሲቪል ሰርቫንት ማፍራት ተቀዳሚው አላማው መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በኋላ እስካሁን በመጣበት አካሄድ መቀጠል የማይችል በመሆኑ፣ እራሱን በመለወጥ ወቅቱ ከሚጠይቀውና ሀገራዊ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በተገቢው ሁኔታ ማገዝ የሚችል እንዲሆን፤ ይህን ተልዕኮም ለመወጣት አዲስ አቅጣጫን መከተል እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ የቀረበው ጥናትም ቀደም ሲል የነበረውን የዩኒቨርሲቲውንና የኮሚሽኑን የተጣረሰ ግንኙነት የሚያስተካከል መሆኑን የገለጹት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የሌለው ሀገር ጠንካራ ሀገር እንደማይሆን በመግለጽ ዩኒቨርሲቲውም እራሱን በመሰረተ- ልማትና በአካዳሚክ ዘርፉም አጎልብቶና አሳድጎ ሀገራዊ ሪፎረሙን መተግበር የሚችል ፣ ሙያውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሲቪል ሰርቫንት በማፍራት ላይ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ሀገራዊ ሪፎርሙን መሰረት በማድረግ ነጻ፣ መንግስት ተሸጋሪ፣ ገለልተኛና ብቁ ሲቪል ሰርቫንትን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አመልክተው፣ ይህን ተልዕኮ መሸከም የሚችል ሲቪል ሰርቫንት በሚፈለገው ደረጃ አለመኖሩ በሂደቱ ላይ ተግዳሮት እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሄ የሚሆነውም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተሸከመው ተልዕኮም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በማመላከት እራሱንም ወደሚፈለገው ስታንደርድ በማሳደግ ልዕቀትን፣ ምሉዕ ሰብዕናን እንዲሁም ፈጠራንና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበት ብሎም ወደ አለም አቀፍ ደረጃ መምጣት እንደሚገባው ዶ/ር መኩርያ ኃይሌ አሳስበዋል፡፡
የኢሰዩ ፕሬዚደንት ዶ/ ንጉስ ታደሰ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የዕለቱ መርሀ-ግብር ተቀዳሚ ዓላማ በዋናነት በሚቀርበው የጥናት ውጤት ላይ ግብዓት የሚሆን የሀሳብ እና በወደፊት የትግበራ ሂደት ላይም የጥናቱን ውጤት በአግባቡ ለመተግበር እንዲቻል ግንዛቤን መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጥናቱም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ሲቪል ሰርቪስ ለማዘመን የተጀመረውን ሪፎርም ለማገዝ እና ዩኒቨርሲቲዎችን በሀገር ደረጃ ያሉበትን ስታንደርድ የመለየት ሂደትን እንደ መነሻ ሀሳብ አድርጎ የተደረገ ጥናት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጥናቱም በከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የአካደሚክ ባለሙያዎች እየታገዘ በመሰራቱ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ከተደረገው ጥናት የተሻለ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሪፎርም የጥናት ውጤትም ዩኒቨርሲቲው የወደፊት አቅጣጫ ምን መምሰል እንዳለበትና የሚመራበትም የህግ ማዕቀፍ የሚያሳይ ዝርዝር ጉዳዮችን ባካተተ መልኩ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በጥናቱ ውጤት እንደተመላከተውም የዩኒቨርሲቲው Public Service and Governance University በሚል ስያሜ እና ቀደም ሲል እንደነበረው ለኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ በመሆን የሚቀጥል ሲሆን ፤ በመሰረታዊነት ሀገራዊ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ሪፎርሙን የሚያግዝ ጠንካራ ሲቪል ሰርቫንት የማፍራት ፣ የትኩረት አቅጫውን በፐብሊክ ሰርቪስ ላይ ያደረገ፣ በማህበራዊ ሳይንስ እና ዲቨሎፕመንት ስተዲስ፣ ፐብሊክ ሴክተር ቢዚንስ እና ምጣኔ ሀብት እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን እና በፐብሊክ ሰርቪስ ኢኖቬሽን በትኩረት የሚሰራ መሆኑን እና የዩኒቨርሲቲው የወደፊት አቅጣጫ ምን መምሰል እንዳለበትና የሚመራበትም የህግ ማዕቀፍ ላይም የአካዳሚክ መዋቅር እና የትምህርት መርሀ-ግብር ቀረጻ፣ የተማሪዎች እና የስታፍ መረጣ፣ የምርምር ፣ የስልጠና እና የማማከር የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን አካቶ ቀርቧል፡፡
በጥናቱ ውጤት ላይም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳብና አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ከመድረክም ለተነሱት ሀሳብና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥተዋል፡፡ የጥናቱ ውጤትን በአግባቡ ለመተግበር እና ዩኒቨርሲቲውን ወደአዲስ ምዕራፍ ለማሻገር በሚደረገው ጥረትም የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴርና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም በሙሉ ኃይል ለማገዝ ያላቸውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል፡፡