በቁልፍ የውጤት አመላካቶች ላይ ማብራሪያ ተሰጠ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (ኢሲሰዩ) ከኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተፈራረመው የዕቅድ አፈጻጸም ውል መለኪያ በሆኑት የቁልፍ ውጤት አመላካቾች (Key Performance Indicators/ KPI) ዙርያ ታህሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ ገለጻ እና ማብራሪያ ተሰጠ፡፡ ገለጻውን የሰጡት የኢሲሰዩ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ሲሆኑ በመርሀ- ግብሩ ላይም የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚደንቶች፣ ዲኖች ፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እና ሥራ አስፈጻሚዎች ተሳትፈዋል፡፡
ፕ/ር ፍቅሬ ለተሳታፊዎቹ ባደረጉት ገለጻም ከኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ጋር ሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንቶች አዲስ በተዘጋጀው የዕቅድ አፈጻጸም ውል የተፈራረሙ መሆናቸውን እና የስምምነት ውሉም ተቋማቱ የተጣለባቸውን ተልዕኮ አፈጻጸም ሊለኩ ይችላሉ ተብለው በተለዩ የቁልፍ የውጤት አመላካቾችን በዝርዝር ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የስምምነት ውሉን መፈራረም አስፈላጊነትም ሲያብራሩ በሀገሪቱ የሚገኙ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደተቋም የተጣለባቸውን ኃላፊነትና ተልዕኮ በመወጣት ረገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ በበርካታ ጉዳዮች የአፈጻጸም ክፍተት እየታየባቸው እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተውጡ ባለመሆናቸው፣ ይህን እውነታ ለመለወጥና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር እንዲኖር የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲም በአምስት መሰረታዊ የትኩረት መስኮች ማለትም በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በአዓለምአቀፋዊነትና ግሎባላይዜሽን እንዲሁም በአመራርና አስተዳደር ላይ ያተኮሩ የየራሳቸው የሆነ መለኪያና መመዘኛ የተቀመጠላቸው ሰማንያ የውጤት አመላካቾችን በመለየት ውል መፈራረሙን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ሰማንያ ርዕሰ ጉዳዮችም በአብዛኛው በዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ጋር የተያያዙ መሆናቸውና እንዴት እንተግብራቸው የሚለውን በጥልቀት በማየት በአግባቡ መተግበር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ቁልፍ የውጤት አመላካቾችንም በዩኒቨርሲቲው ያለበትን ደረጃ የተተገበሩ፣ በመተግበር ላይ ያሉ እና ገና ያልተጀመሩ በሚል በሶስት ደረጃ በመክፈል ያሳዩት ፕ/ር ፍቅሬ ከየዘርፍ ኃላፊዎች ጀምሮ ሁሉም በየደረጃው የእያንዳንዱን የውጤት አመላከች የያዘውን ጽንሰ-ሃሳብ በአግባቡ ተገንዝቦ በቀሪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ መፈጸም እንደሚጠበቅበት እንዲሁም በተዘረጋው የክትትል እና የድጋፍ ስርዓት መሰረት በየደረጃው ሪፖርት የሚደረግ መሆኑን፣ የሚቀርበውም ሪፖርት እውነተኛ እና ተአማኒነት ያለው፣ በአግባቡ ተሰንዶ የሚቀርብ መሆን እንዳለበት ገልጸው እነዚህ የውጤት አመላካቾችን ለይቶ በተገቢው ደረጃ መፈጸም የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብም ሆነ የተቋሙን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ዐብይ ጉዳይ በመሆኑ፣ ቁልፍ የአፈጻጸም አመላካቾች ውል በተሰጡን ተግባራት ትኩረት አድርገን ስራዎችን እንድንሰራ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩ ገልጸዉ፤ በጥንቃቄና በትጋት ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ አስፋላጊ መሆኑን በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙ የስራ ኃላፊዎችም በቀረበው ገለጻ ላይ ያላቸውን ጥያቄዎችና አስተያየቶች እንዲሁም ሊሟሉ ይገባሉ ያሏቸውን ግብዐቶች በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ፕ/ር ፍቅሬ ለጥያቄዎቹ ማብራርያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡