በኢሲሰዩ የራስ-ገዝነት ረቂቅ የሽግግር ሰነዶች ላይ ሶስተኛ ዙር ውይይት ተካሄደ፡፡
የኢትዮጲያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለራስ-ገዝነት ሂደቱ መደላድል እንዲሆኑ በተዘጋጁት ረቂቅ ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ/ም የጀመረውን ውይይት ሶስተኛ ዙር ዉይይት ታህሳስ 11 ቀን 2017 ዓ/ም ተካሄደ፡፡
የዕለቱ ውይይት ያተኮረው በምርምርና ትብብር ዘርፍ ስር “የኢሲሰዩ የምርምር አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ “፣ “የኢሲሰዩ የምርምር በጀት ድጋፍ አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ “ እና “የኢሲሰዩ የተመራቂ ተማሪዎች ምርምር ማስተባበሪያና ድጋፍ ረቂቅ መመሪያ “ በሚሉት ሰነዶች ላይ ነው፡፡ በህዳሴ አዳራሽ በተካሄደው ውይይት ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች እና የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርስቲዉ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ዳሳለኝ የቀደሙትን ሁለት ውይይቶች ውጤታማነት አስታውሰው፣ የዛሬው ውይይት የዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ ምሶሶ እና እስትራቴጂካዊ ዘርፍ በሆኑት በምርምርና ማማከር ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በማስከተለም “የምርምር እና የማማከር ሥራዎች የዩኒቨርሲቲያችንን ህልውና የሚወስኑ ሲሆኑ እንደ አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መቀጠል ካለብን የምርምርና የማማከር ሥራን በጥራት እና በዓለምዓቀፋዊ ስታንዳርድ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል ፡፡ በምርምርና ማማከር ሥራ የቀጨጨ ዩኒቨርሲቲ፣ ዩኒቨርሲቲ ሊባል አይገባውም፤ ተፈላጊም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሊሆን አይችልም፡፡” ብለዋል፡፡ አክለውም፣ ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ተቋማት የሚለየው፣ ጠንካራ የምርምር ውጤት ሲያፈልቅ መሆኑን ገልጸው፣ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሚቀርቡት ሶስት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
ቀጥሎም “የኢሲሰዩ የምርምር አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ” በዶ/ር ዘሪሁን ዶዳ የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ “የኢሲሰዩ የምርምር በጀት ድጋፍ አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ” በዶ/ር ሙከሪም ሚፍታህ የግራንት ማፈላለግና ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና “የኢሲሰዩ የተመራቂ ተማሪዎች ምርምር ማስተባበሪያና ድጋፍ ረቂቅ መመሪያ” በዶ/ር ታረቀኝ ዲኣ የድረ ምረቃ ምርምር አስተባባሪ ቀርቧል፡፡
በማጠቃለያውም የዩኒቨርስቲዉ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ የተነሱት ሀሳብ እና አስተያየቶች ለቀረበው እረቂቅ መመሪያ በማዳበሪያነት የሚያገለግሉ ግብዓቶች ስለሆኑ መውሰድ እንደሚገባ ለአዘጋጆቹ ማሳሰቢያ ሰጥተው፣ ከተሳታፊዎች ለቀረቡት ጥያቄዎች የበኩላቸውን ምላሽ ከሰጡ በኋላ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡