በኢሲሰዩ የራስ-ገዝነት ረቂቅ የሽግግር ሰነዶች ላይ ዉይይት ተካሄደ
የኢትዮጲያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር በተቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት ወደ ራስ-ገዝነት በሚያደርገዉ ጉዞ ሁለተኛ ምዕራፍ ሂደት ላይ ደረሰ፡፡ በዚህም በዋናነት ለራስ-ገዝነት ሂደቱን መሰረት የሚሆኑ፣ የተለያዩ ህጎች ፣ መመሪያዎች እና ፖሊሲዎች የተዘጋጁ ሲሆን ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ “የኢሲሰዩ የተማሪዎች ምልመላ፣መረጣና ቅበላ ረቂቅ ፖሊሲ” ላይ ግምገማዊ ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡
በዚህ ግምገማዊ ወርክሾፕ መግቢያ ላይ የዩኒቨርስቲዉ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ዳሳለኝ እንደገለጹት በመላው አገሪቱ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በአብዣኛው በለውጥ ሂደት ውስጥ እያለፉ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ከእነዚህ ለውጦች መካከል አንዱ የዩኒቨርሲቲዎችን የመምራት እና የአስተዳደር ሥርዓትና ማዕቀፍ የመቀየር ለውጥ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ እንደ ወሳኝ ጉዳይ የሚጠቀሰውም የተቋማት ራስ-ገዝነትን ማስፈን መሆኑን አንስተው ራስ-ገዝነትም ለተቋማት እራሳቸውን በተሻለ እንዲያስተዳድሩ ቀድሞ ከነበረው ከፍ ያለ በህግ የተቀመጠ ነጻነትን እንደሚሰጣቸው፤ ብሎም ሀብትን የመፍጠርና የማንቀሳቀስ፤ በዚህም የተሻለ ጥራት ያለውና ተወዳደሪ የትምህርት ተቋም እንዲሆኑ ማስቻልን ዐላማው ያደረገ የለውጥ እሳቤ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጲያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ከሚገኙ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በምርምር ዩኒቨርሲቲ ምድብ ውስጥ የተመደበ እንደሆነ በመግለጽ ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር በተቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት በ2018 ዓ.ም ከጥገኝነት ምዕራፍ በመላቀቅ ወደ ከፊል ራስ-ገዝነት በመሸጋገር በተላይ አካዳሚያው የሆኑ ነጻነቶችን እንጎናጸፋለን ፤ ከእነዚህ አካዳሚያዊ ነጻነቶች መካከል አንዱ ተማሪዎችን በራሳችን መስፈርት መሰረት መልምለንና መርጠን የመቀበል መብት ይኖረናል ብለዋል፡፡
በተለይ ወደ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ በሚደረገዉ ጉዞ በተቋሙ ባለፉት ዓመታት የሪፎርም ዕቅድ በማዘጋጀት የተለያዩ ስራዎች እንደተሰሩ ያስታወሱት ፕ/ር ፍቅሬ ለውይይት የቀረበው የተማሪዎች ምልመላ፣ መረጣና ቅበላ ረቂቅ የፖሊስ ሰነድም ለዩኒቨርሲቲው የራስ-ገዝነት ጉዞ አንድ ወሳኝና መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ቀድሞ እንደነበረው ከሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ተማሪዎችን በስኮላር ሺፕ የመቀበሉ ሂደት እንዳለ ሆኖ ከሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ውጪ ያሉትንም በክፍያ እና ከሀገር ውጪም የሚያመለክቱ ተማሪዎችን የምንቀበልበትን ህግና መስፈርት የሚይዝ ፖሊሲ ነው ብለዋል፡፡
ሌላው የአካዳሚክ ነጻነት ጋር ተያይዞ የሚታየው ዩኒቨርሲቲ የራሱ የሆነ የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያና አዋጭና ተመራጭ የሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞችን የመቅረጽ እና የማስጀመር ነጻነትን የሚሰጠው የውስጥ ጥራትን የማስጠበቅ ሂደት ነው፡፡ ይህን በሚመለከት የተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲም በቀጣይ በስፋት የምንመለከተው ሲሆን እነዚህን ነጻነቶችም በመጀመሪያው ዙር የምንጎናጸፋቸው ነጻነቶች ይሆናሉ ብለዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ሀብት የማፍራት፣ በራስ ገቢ የመንቀሳቀስ የፋይናንስ ነጻነት፣ ብቃት ያለው ስታፍ የማደራጀት እና መዋቅራዊ ነጻነቶች እንደ ተቋም ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ የሚጎናጸፋቸው ነጻቶች እንደሚሆኑ ፕ/ር ፍቅሬ ገልጸዋል፡፡
በግምገማ መድረኩም “የኢሲሰዩ የተማሪዎች ምልመላ፣መረጣና ቅበላ ረቂቅ ፖሊሲ” በዶ/ር ተመስገን ቢረጋ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በቀረበው ረቂቅ ፖሊሲም ለመጀመሪያ ዲግሪ ፣ ለሁለተኛ ዲግሪና ለሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች አጠቃላይ ከምዝገባ ጀምሮ እስከ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ድረስ ያለው ሂደት እና መስፈርት በዝርዝር ተካቶ ቀርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የውጪ ሀገር አመልካቾችም በዩኒቨርሲቲው ለመማር የሚያስፈልጋቸውን መስፈርቶች በዝርዝር ተካተዋል፡፡
በቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ ላይም ከተሳታፊዎች በርካታ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አመልካቾችን በዕድሜ የመገደብ ሁኔታ፣ የባንክ ሂሳብ እንዲቀርብ መጠየቅ፣ በአንድ ጊዜ ሁለት በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች መማርን በተመለከተ፣ ምዝገባንና ቅበላን በኦንላይን የማድረግ ሂደት፣ ተማሪዎችን የመለየት ሂደት እና ሌሎች በርካታ ሀሳቦች ተነስተው ቤቱ በስፋት ተወያይቶባቸዋል፡፡
በማጠቃላያዉም ላይ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ዩኒቨርሲቲዉ ወደራስገዝነት በሚያደርገዉ ጉዞ እንደነዚህ አይነት ፖሊሲዎችን በአግባቡ መገምገም እና መተቸት ትልቅ ፋይዳ እንዳለዉ ገልጸዉ፣ ተሳታፊዎችን በማመስገን የተነሱትን ሀሳቦች እንደ ግብዐት እንደሚወስዱ እና አስተያየቶቹን በማካተት ለሴኔት ቀርቦ የሚጸድቅ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይ በሚደረገዉ የሌሎች ረቂቅ ፖሊሲዎች ግምገማ ላይ የዩኒቨርስቲዉ ማህበረሰብ የሚያደርገውን ተሳትፉ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡