በኢሲሰዩ የስልጠና ኢንስቲትዩት አዳዲስ የተመደቡ አመራሮች ጋር የትውውቅ መርሀ ግብር ተደረገ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ከሚገኙት የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መመደቡን ተከትሎ በተዘጋጀው አዲስ የአደረጃጀት መዋቅር መሰረት በዩኒቨርሲቲው የስልጠና ኢንስቲትዩት ስር ለሚገኙ የስራ መደቦች ለተመደቡ አዳዲስ አመራሮች በመጋቢት 11ቀን 2015 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ ትውውቅ መርሃ ግብር አዘጋጀ፡፡
በትውውቁ መርሀ ግብሩ ላይም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ በአዳዲስ የስራ መደቦቹ ላይ ለተመደቡት አመራሮች ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግርና በሰጡት የስራ መመሪያ ላይ በአዲሱ አደረጃጀት መሰረት የስልጠና ኢንስቲትዩቱ በዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ መሰረት ለፌደራል ተቋማት እና ለአዲስ አበባ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ ተቋማት አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት አቅማቸው የመገንብት ኃላፊነት አንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
በዚህም ኢንስቲትዩቱ የስልጠናዎችን ጥራት ፣ተደራሽነት፣ ተገቢነት እና ወቅታዊነት ከማረጋገጥ በተጨማሪም ከፌዴራልና ከክልል ተቋማት የሚመጡ የስልጠና ፍላጎቶች ጥያቄን በአግባቡ ማስተናገድና የምስራቅ አፍሪካ የፐብሊክ ሰርቪስ ተቋማትና ሰራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግና ተግባራዊም ማድረግ የየስልጠና ኢንስቲትዩቱ የተልዕኮ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕ/ር ፍቅሬ አክለውም የስልጠና ኢንስቲትዩቱ የኢፌዴሪ የፌዴራል ተቋማት መስሪያ ቤቶችን አደረጃጀት መዋቅርን መሰረት በማድረግ በስልጠና ኢንስቲትዩቱ ስር ያሉ የአካደሚ ሰራተኞች በቡድን በማደራጀትና ለእያንዳንዳቸውም አስተባባሪ በመመደብ የስልጠና አሰጣጥ ሂደቱ የሚሻሻል መሆኑን አመልክተው ፤ የስልጠና ኢንስቲትዩት በሰው ኃይል ደረጃም እራሱን እንዲችልና እጥረት ባለበት መስኮች ላይ ብቻ የተባባሪ አሰልጣኞች ቅጥር የሚካሄድ መሆኑን እንዲሁም በ2022 መጨረሻ ላይ አሁን ያሉት 6 (13.9%) የፒኤችዲ ምሩቃን 50%እና ከዚያ በላይ ለማድሰር ይሰራል ብለዋል፡፡
ፕ/ር ፍቅሬ በተጨማሪም በሰጡት የስራ መመሪያ መሰረት የስልጠና ኢንስቲትዩቱ የትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ሰራተኞች የስራ ስምሪት መሰረት በኢኒስትቲዩቱ የሚሰሩ የአካዳሚክ ሰራተኞች እያንዳንዳቸው 60% የስልጠና ፣ 25% የምርምር እና 15% የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ፤ የሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎትም በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር በየካ፣ በቦሌ፣እና ለሚኩራ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም በለገጣፎ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ ተቋማት እንደሚሆን ገልጸው፤ የስልጠና አገልግሎቱንም ለማሳደግም በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮችን በመለየት ልዩ የስልጠና ፕሮግራሞችን ማልማት፣ በዩኒቨርሲቲው የ10 ዓመት ስትራቴጂ እቅድ መሰረትም የ ኢ- ሰርቪስ አገልግሎት አሰራር ላይ የስልጠና ፕሮግራም በመቅረጽ ተግባራዊ ማድረግ፤ ሰልጣኞችን የሚያሳትፉ ተቋማት ቁጥርን ማሳደግ፣ ስልጠናዎችን ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ብቃት ተኮር አሰራር ጋር አስተሳስሮ ተጋባራዊ ማድረግ ፣ የወጣቶች የስልጠና ፕሮግራም አፈጻጸምን ማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሰሩ የሚገቡ ተግባራት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ስልጠና ኢንስቲትዩት ምርምርን ህትመት አፈጻጸም ማሻሻልን በተመለከተም የኢኒስቲትዩቱን የምርምር ጋዜጣ ህትመት ማስጀመርና ሳይቆራረጥ እንዲቀጥል ማድረግ እንዲሁም የተለዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሴሚናር እና ወርክሾች ማካሄድ ፣ ራስ ገዝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የመሆን ዕቅድን ለማሳካት ከስልጠና አገልግሎት የሚገኝ የውስጥ ገቢ መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ዝርዝር ዕቅድ ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ ፣ የስልጠና ፋሲሊቲዎችንም ለስልጠና አገልግሎት ብቻ በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር የስልጠና መገልገያዎቹንም የበለጠ የማስፋፋትና የማዘመን ስራ የሚሰራ እና ወደፊትም ለኢኒስቲትዩቱ ዘመናዊ የስልጠና ህንጻ ግንባታ የሚካሄድ መሆኑን እንዲሁም ለ2016 በጀት ዓመት ለኢኒስቲትዩቱ በቂ በጀት የሚመደብ ቢሆንም ኢኒስቲትዩቱ ከሀገረ ውስጥና ውጭ ከሚገኙ አቻ ፣ ረጂና የልማት ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ለሚያካሂዳቸው የስልጠና ፕሮጀክቶች ተጨማሪ ሀብት ማግኘት እንደሚገባው ፕ/ር ፍቅሬ በሰጡት የስራ መመሪያ ላይ አመላክተዋል፡፡
በመጨረሻም ከአመራሮችና ከአሰልጣኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ በመስጠት ለአዳዲስ አመራሮችም መልካም የስራ ዘመን ተመኝተው፤ አመራሮቹም ዩኒቨርሲቲው በዋናነት ስልጠና የሚሰጥ ዘርፍ እንደመሆኑ ሙሉ ዝግጅት በማድረግ ስራቸውን በታላቅ ኃላፊነት ተቀብለዉ እንዲሰሩ ያሳሰቡ ሲሆን ቀደም ሲል የስልጠና ዘርፉንን የስልጠና ማዕከላትን ሲመሩ ለነበሩ የቀደሞ አመራሮችም ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡