በኢሲሰዩ የትምህርት ተቋማት እውቅና ማግኘት የሚችሉት በብቃት ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት መሰረት ስለመሆኑ ማብራሪያ ተሰጠ፡፡
የኢሲሰዩ ካውንስል ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ/ም ባካሄደው የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድና የ1ኛ ሩብ አመት የሪፎርም የስራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ፣ የከፍተኛ ትምህረት ተቋማት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን እውቅና ለማግኘት፣ ከሙጁላር የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ወጥተው፣ በብቃት ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት (Outcome based education system) ማስተማር እንዳለባቸው ለካውንስሉ አባላት ማብራሪያ ተሰጠ፡፡
ማብራሪያውን የሰጡት የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ደ/ር አድማሱ ቴሶ ሲሆኑ፣ እስካሁን ያለውን ሙጁላር የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት፣ አሁን ከምንከተለው ብቃት ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ጋር ሲነጻጸር፣ ሙጁላር የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት፣ ምሩቃንን በማፍራት ላይ የሚያተኩር በመሆኑ፣ ተማሪው የያዘውን እውቀት እና ክህሎት እንደማይለካ ገልጸዋል፤ በአንጻሩ ብቃትን መሰረት ያደረገው የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት (Outcome based education system) ምሩቃንን ከማፍራት ባለፈ፣ ተማሪው በየፕሮግራሙ፣ የእውቀት፣ የክህሎት እና የአመለካከት ለውጥ ማምጣቱን መለካት የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሙጁላር የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ተማሪን ካስመረቀ በኋላ የሚከታተልበትን ስርዓት ያልዘረጋ ሲሆን፣ አዲሱ የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ግን፣ ተማሪው ተመርቆ ከወጣ በኋላ ባሉት አምስት አመታት ውስጥ፣ ያመጣውን ውጤት ለመለካት እና ለመገምገም የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል፡፡
በዚህ በብቃት ተኮር የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት (Outcome based education system) ማንኛውም ተግባር በዘፈቀደ የማይሰጥ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ተግባር የሚመጣው ውጤት፣ መምህሩን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት እንዳለውም በማብራሪያቸው ገልጸዋል፡፡ አክለውም ይህ ማብራሪያ ለጠቅላላው የካውንስሉ አባላት እንዲሰጥ የተደረገበትን ምክንያት ሲያብራሩ፡- “የትምህርት ጥራት ጉዳይ የአንድ ትምህርት ክፍል ወይም የአንድ ዳይሬክቶሬት ወይም የአንድ ምክትል ፕሬዘደንት ጉዳይ አይደለም፤ ሁሉን አቀፍ አካሄድን ይጠይቃል፤ የትምህርት ጥራት በአንድ የስራ ክፍል የሚመጣ አይደለም፤ ነገር ግን በአንድ የስራ ክፍል ሊጨናገፍ ይችላል፡፡” ብለዋል፡፡
ሌላው ማብራሪያ የተሰጠበት ጉዳይ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አዲስ የትምህርት ፕሮግራም ሲቀርጹም ሆነ ነባሩን ሲከልሱ፣ በዋናነት ለትምህርት ተቋሙ የተሰጠውን ልየታ መሰረት በማድረግ፣ የትምህርት ፕሮግራም ቀረጻን አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን መመሪያ በመከተል፣ በሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ማእቀፍ በማገናዘብ፣ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ያወጣውን መመሪያ በመከተል እና የፍላጎት ዳሰሳ አድርጎ በገለልተኛ አካል በማስገምገም መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ማብራሪያው ካበቃ በኋላ በካውንስሉ አባላት እውቅና የማግኘት ሂደቱን ከተቋም መጀመር ይሻላል ወይስ ከትምህርት ፕሮግራም መጀመር ይሻላል? የሚሉት ሀሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ፣ በሰጡት ማጠቃለያ እውቅናን ለማግኘት ከተቋም ለመጀመርም ሆነ በትምህርት ፕሮግራም ለመጀመር የተለያየ መስፈርት እንዳለው ገልጸው፣ “ዋናው ቁም ነገር ስራውን አክብደን ማዬት የለብንም፤ በእኛ አቅም ልንሰራው የምንችለው መሆኑን ተገንዝበን መንቀሳቀስ አለብን፡፡” ብለዋል፡፡