በኢሲሰዩ የአዲስ ምዕራፍና የለውጥ ጉዞ ሂደትን አስመልክቶ ለተለያዩ የሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ፡፡
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (ኢሲሰዩ) የወደፊት አቅጣጫ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሪፎርም ጥናት ውጤት እና የዩኒቨርሲቲው የወደፊት አዲስ የለውጥ ጉዞ ሂደትን አስመልክቶ ለተለያዩ የሚዲያ አካላት ኢሲሰዩ ፕሬዚደንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ መስከረም 22 ቀን 2018 ዓ.ም በሴኔት አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫውም ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ሶስት አሰርት ዓመታት የሀገሪቱን የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት በትምህርትና በስልጠና አቅማቸውን ሲገነባ የቆየ መሆኑን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሁለተኛውን ምዕራፍ የለውጥ ጉዞ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ ጉዞውም ዩኒቨርሲቲው ምን መምሰል እንደሚገባው እና በምን መልክ ሊደራጅ እንደሚገባው የሚያጠና ሀገራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለዘጠኝ ወራት ባደረገው ጥናት ዩኒቨርሲቲው በአዲስ መልክ ለመደራጀት በሚያስችሉት የዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮ፣ የትኩረት አቅጣጫ፣ የሚመራበት ፍልስፍና እና እሴቶችን የመለየት ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸው በጥናቱ ውጤት መሰረትም ዩኒቨርሲቲው በተግባራዊ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ምድብ ስር የተካተተ መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ተልዕኮም ብቃትና ጥሩ ሥነ-ምግባር ያለው ምሩቃንን ማፍራት እና የፐብሊክ ሴክተሩን በፈጠራ፣ ዲጂታላይዜሽን እና በስልጠና የተቋማትን አቅም መገንባት መሆኑን ገልጸው የትኩረት አቅጣጫውም በአመራርና አስተዳደር፣ በፐብሊክ ሰርቪስ ሪፎርም፣በማህበራዊ ሳይንስና ማህበራዊ ልማት ፣ በፋይናንስና ኢኮኖሚክስ፣ በህግና በዲጂታላይዜሽንና ፈጠራ ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ በጋዜጣዊ መግለጫቸው አመላክተዋል፡፡
በጥናቱ ውጤት መሰረትም የአካዳሚክ ፕሮግራሞች የተለዩ መሆናቸውን ጠቅሰው የፐብሊክ ሴክተር የሪፎርም ሥራዎችን የሚያግዝ ማዕከል እና ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የስልጠና ማዕከል ለማቋቋም እንዲሁም አጠቃላይ የሪፎርሙ ጉዞ ማስፈጸሚያ ዕቅድ በስፋት እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው የመንግስት ተቋማትን በፈጠራና በኢኖቬሽን የማገዝ፣ የተማሪዎች ምንጩም ከሲቪል ሰርቪስ ተቋማትና ከአስራ ሁለተኛ ክፍል ተፈታኞች በቀጥታ መቀበል መቻሉ እንዲሁም በትምህርት ፕሮግራሞች አደረጃጀት ማለትም በጋራ ኮርሶች፣ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የማይሰጥ ነገር ግን በዚህ ዩኒቨርሲቲ ብቻ የሚሰጥ ፋውንዴሽናል ኮርሶች መኖሩ እና በሙያዊ ኮርሶች መደራጀቱ ዩኒቨርሲቲውን ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ልዩእንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆናቸውንና በአሁኑ ወቅትም የዩኒቨርሲቲው በትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች ምርጫ መካተቱን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲው የመጨረሻ መዳረሻም ራስ -ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡