በኢሲሰዩ የዕጩ ዲፕሎማቶች ስልጠና ተጀመረ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጪ ጉዳይ ስልጠና ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር ስድስተኛው ዙር የዕጩ ዲፕሎማቶች ስልጠና ጀመረ፡፡ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም በተደረገው የስልጠና መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይም ክቡር ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር በመገኘት ከሰልጣኖችጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በስልጠናው መክፍቻ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ንጉሥ ታደሰ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የሲቪል ሰርቫንቱን አቅም ለመገንባት የተቋቋመ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ከምስረታው ጀምሮ በርካታ ለሀገር ባለውለታ የሆኑ አመራሮችንና ባለሙያዎችን ያፈራ እና አሁንም በማፍራት ላይ ያለ ተቋም መሆኑን አስታውሰው ከማንኛውም የመንግስት ተቋም ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለፉት ዓመታትም ከኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋርም ጠንካራ ግንኙነት ያለው መሆኑንና ያለፉት አምስት ዙር ስልጠናዎችም በስኬት እንዲጠናቀቁ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን አስታውሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ፕሮግራምን በመክፈትና ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።ስድስተኛውን ዙር የዕጩ ዲፖሎማቶች ስልጠናን አስመልክተው እንደተናገሩት ሰልጣኞች በዩኒቨርሲቲው በሚኖራቸው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን አመራሩ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደረግ ገልጸዋል፡፡
በስድስተኛው ዙር ስልጠናም ሃምሳ ዕጩ ዲፖሎማቶች ለአራት ወራት ስልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከልም ሰላሳ አንድ ሰልጣኞች ሴት ዕጩ ሰልጣኞች ሲሆኑ በአጠቃላይ ሰልጣኞቹም በመጀመሪያው ዙር የፖሊሲ ስልጠና እንዲሁም በቀጣዩ የአካዳሚክና ተግባር ተኮር ሰልጠና የሚወስዱ እንደሚሆን ከመድረኩ ተገልጿል፡፡