በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ‘‘በሀገረ-መንግስት ግንባታ የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የነበረዉ ዉይይት ተጠናቋል
በኢሲሰዩ ‘‘በሀገረ-መንግስት ግንባታ የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ለ 4 ቀናት በሁለት ዙር ከዩኒቨርስቲዉ የአካዳሚክ ሰራተኞች ፣የአስተዳደርዘርፍ ዳይሬክተሮች እና ከቡድን መሪዎች ጋር ሲካሄድ የነበረዉ ዉይይት ተጠናቋል፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተመስገን ቡርቃ ስለውይይቱ አስፈላጊነት ሲያብራሩ አሁን ባለው የዓለማችን ነባራዊ ሁኔታ ከምንግዜውም በላቀ ሁኔታ ሀገራት በጥንቃቄ የሚመሩበት መሆኑን አመልክተው ሀገራችን ኢትዮጵያም ካለችበት የጂኦፖለቲካል ሁኔታ ካላት የዳበረ ታሪክና የሰው ሀብት እንዲሁም በዓለማችን ላይ ያሉ ትላልቅ ሀገራት በዙሪያችን የጦር ሰፈር የመገንባት እንቅስቃሴና የራሷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በምታደርገው ጥረት እየደረሰባት ባለው ተፅዕኖ ምክንያት ምሁራን ሊወጡት የሚገባው ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በዚህም ረጅም የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ያለው ሀገር በአንዳንድ ክስተቶች ሀገር ችግር ውስጥ የሚገባበት ምክንያት ምንድን እንደሆነ፣ በትምህርት ስርዓታችን ውስጥም ምን እንደጎደለ እንዲሁም ውስጣዊ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ምሁራን የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ የሚያደረግ ውይይት መሆኑን በማስገንዘብ ተሳታፊዎች በውይይቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አሳስበዋል፡፡
ፕ/ሮ ፍቅሬ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ለውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች እንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በማስከተልም ምሁራን ለሀገር ስልጣኔና ዕድገት ጉልህ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን በማብራራት የሀገራችን መፃኢ ዕድል በእጃችን ላይ እንዳለ በመገንዘብ ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታችንን መወጣት ይገባናል ብለዋል፡፡ ‘‘ምሁር ለሌላዉ ትሩፋት መሆን አለበት” ሀገር የሚገነባዉ በተቋም ነዉ፤ ተቋም በሌለበት ሀገር የለም ለዚህ ደግሞ ምሁራን ሀላፊነት አለብን ብለዋል ፡፡
በመቀጠልም በሁለት ዙር በዶ/ር ለማ ጉዲሳ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ‹‹በሀገረ መንግስት ግንባታ የምሁራን ሚና›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሀገራዊ ሰነድ ቀርቦ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በስፋት ተወያይተውበታል፡፡
የውይይት መድረኩን በዚህ ወቅት ለማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሀገር ያለንን አቅም ሁሉ አስተባብረን በጋራ ቆምን ሀገራችንን ለማበልፀግ፣ በምሁራን አማካይነትም መጪውን ውስብስብና የውድድር ዓለም እንዴት አሸናፊ ሆኖ መውጣት እንደሚቻል መፍትሔ ማማልከት እና እንደ ሀገር ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተገኙ ስኬቶች የነበሩና የቀጠሉ ርብርብ የሚሹ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት መወያየት አስፈላጊ መሆናቸው በዶ/ር ለማ ጉዲሳ በቀረበው ዶክመንት ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዶክመንቱም በሀገሪቱ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ያጋጠሙ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች የቀረቡ ሲሆን በቀጣይ ሥራዎች ላይ የምሁራን ሚና በዋናነት ሊያተኩርባቸው የሚገቡ እንደ የፖለቲካ ገበያን መገንዘብና በሀገር ላይ የተደቀነውን ፈተና መታገል፣ የፖለቲካ ገቢያ ተፅዕኖ እና የኒዮፓትሪሞኒያሊዝም ጋብቻ ፣ የአክራሪነትና የፖለቲካ ገበያ ትስስር፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ገበያ አዝማሚያ፣ ዘላቂ አወንታዊ ሰላምና ስልጡንና ዲሞክራቲክ ማህበረሰብ መገንባት እና ሌሎችም ሀሳቦች በስፋት ተነስተዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በብርቱ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈችን ሀገር ረጅም ዘመን የመንግስት ታሪክ ባለቤት በሆነች ሀገር ውስጥ የሀገር መንግስት ግንባታ ያልተጠናቀቀው ምን ቢጎድለን ነው፡፡ ላሊበላ፣ አክሱም፣ ጎንደርን ወዘተ የሰሩ ሰዎች የነበሩባት ሀገር እንዴት ለዘመናት የሚሻገሩ ህንፃዎችንና መንገዶችን የሚሰሩ መሀንዲሶችን ማፍራት ተሳናት ? በጋራ ሞተው ሀገር የሚታደጉ ዜጎች ባሉበት ሀገር እንዴት በጋራ ቆመን ከድህነት መውጣት ተሳነን ? ኢትዮጵያ ባሏት እሴቶች የሚኮራ ትውልድ እንዴት ሁል ጊዜ የመጤ ሀሳብና ርዕዮተ-ዓለም እየተጨቃጨቀና እየተከራከረ ሀገር ለማፍራት ይታትራል? እንዲሁም ለኢትዮጵያ መለወጥ ዋጋ ከፍሎ ዕድል ፈጥሮ ሲያበቃ የተገኘውን ዕድል ገፍቶ ወደ ተሟላ ድል መቀየር እንዴት ለተደጋጋሚ ጊዜ ይከብዳል? በሚሉ ዓበይት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት የተደረገ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ምሁራንም ከላይ በተነሱ ርዕሰ-ጉዳዮችና በሌሎችም ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይትና ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን በተነሱት ሀሳቦችና ጥያቄዎችም በዉይይተቶቹ መድረክ ማጠቃለያ ላይ ክቡር ዶ/ር ቀነአ ያደታ የመንግስት ተወካይና ዶ/ር ተመስገን ቡርቃ የኢ.ሲ.ሰ.ዩ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ምላሽ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም አወያዮቹ ክቡር ዶ/ር ቀነአ ያደታ እና ዶ/ር ተመስገን ቡርቃ እንዳሉት መንግስት ወደፊት ተከታታይ የዉይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ችግሮችን በዉይይት ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን በመግለጽ እንዲህ አይነት መድረክ በቀጣይነት ስርአት ተበጅቶለት ተቋማዊ በማድረግ በቋሚነት እንደሚቀጥል ገልጸዋል ፡፡ዉይይቱም በስኬት በመጠናቀቁ ለተሳታፊዎቹ ምስጋና አቅርበዋል፡፡