በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን ተከበረ
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረውን የጸረ ሙስና ቀን ‘‘ሙስና ጠላታችን ነው ፤በጋራ እንታገለው’’ በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርስቲዉ ሰራተኞች እና አመራሮች በተገኙበት ህዳር 26 ቀን 2016 ዓ/ም በፓናል ውይይት እና በተቋሙ በስጋት አስተዳደር ላይ የተካሄደ የጥናት ግኝት በማቅረብ ተከብሯል፡፡
የውይይቱን መድረክ የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ በአስተላለፉት መልዕክት ‘‘ ሙስና ግዑዝ ነገር አይደለም ፤ሀብት በአግባቡ ለታለመለት ጉዳይ አለማዋል ማለት ነዉ ፡፡በዚህም አመራሮች የመወሰን ስልጣን ያለን የመንግስት ሀብት በአግባቡ እየተጠቀምን ነዉ ወይ የሚለዉን መጠየቅ ፣ተቋማችንን እያየን በመገምገም አቅጣጫ እያስቀመጥን የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የጸረ ሙስና ትግል አካል ሆነን እነደ ዜጋ ድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል ፡፡’’
ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ጽሁፍ በስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሰላማዊት ተ/ሚካኤል ‘’የሙስና ምንነትና የሚያስከትለው ጉዳት’’ በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የስራ ክፍሎች በስጋት አስተዳደር ላይ የተካሄደ የጥናት ግኝት ቀርቧል፡፡ በውይይቱም የሙስና ምንነት ፤ መንስኤዎችና መገለጫዎቹ፤ ሙስና የሚያስከትለው ጉዳት እንዲሁም ሙስናን በጋራ ለመከላከል የባለ ደርሻ አካላት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ለተሳታፊዎች በዝርዝር ቀርቧል ፡፡
በእለቱም በየዘርፉ ያሉ ኃላፊዎች የሙስና ተጋላጭነት እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚታገሉት የዘረጉት አሰራር ጭምር አብራርተዉ ለሙስና ሂደት በር የሚከፍቱ አሰራሮች እንዴት እንደሚከታተሉ አስተያየታቸዉን በመስጠት የዘርፋቸዉን ሂደት ገምገመዋል፡፡በተለይ ከፍተኛ ፋይናንስ የሚያንቀሳቅሱ እና የሰው ሀብትን የሚመሩ ስራ አስፈጻሚዎች፣ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ከመታገል አኳያ እራሳቸውን እንዲፈትሹ በቀረበው የውይይት ርዕስ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በአንዳንድ ስራ አስፈጻሚዎች በተጨባጭ የተሰራው ስራ እና የታየው የፀረ ሙስና ትግል ቁርጠኝነት ለሁሉም ስራ አስፈጻሚዎች በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በማጠቃላያዉም ላይ ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት ይህ መድረክ የምንማማርበት ግንዛቤ የምንጨብጥበት መድረክ እንደመሆኑ ሁላችንም በተሰማራንበት እና አመራር በምንሰጥበት ዘርፍ ስራዎች በአግባቡ መሰራቱን የማረጋገጥ ትልቅ ሀላፊነት እንዳለብን ከዚህ ባለፈም ለምንስራቸዉ ማንኛዉም ስህተቶች ከተጠያቂነት እንደማናመልጥ መገንዘብ ማንኛዉም ስራዎች በህግ እና በህግ አግባባብ ብቻ መስራት አስፈላጊ ነዉ ብለዋል፡፡