በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከበረ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ 18ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀን “ ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት“ በሚል መሪ ቃል ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ ተማሪዎችን እና ሰራተኞች በተገኙበት በፓናል ውይይት እና የጥያቄና መልስ ዉድድር በማድረግ አከበሩ፡፡
የፓናል ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታዴዎስ ሜንታ እንደተናገሩት ይህ በዐል በዋናነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር የባህል ትዉዉቅ ከመፍጠሩም በላይ የሕዝቦችን ወንድማማችነት በማጠናከር ሕብረ ብሔራዊ አንድት ለማጎልበት ትልቅ ሚና እንደሚኖረዉ በመግለጽ በዓሉ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች እርስ በእርስ ከመተዋወቃቸዉ ባሻገር የእርስ በእርስ መቀራረብ የሚፈጠርበት ትልቅ ኩነት እንደሆነ አብራርቷል፡፡ ሀገራችን በርካታ መገለጫዎች ያሏቸው ከ80 በላይ ብሄሮች ብሄረሰቦች ያሉባት ሀገር እንደመሆኗ የህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓት በጠንካራ ሂደት መገንባት ለሀገር እድገት እና ሰላም ግንባታ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የፌደራሊዝም ጥናት ትምክርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ግሩም ክንፈሚካኤል ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ በጽሁፋቸው ኢትዮጵያ እስከ አሁን ድረስ የተገበረቻቸዉን የመንግስት አወቃቀር በመዳሰስ በአሁን ወቅት እየከተለቸዉ ያለዉን የሕብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት አብራርተዋል፡፡ በቀረበው የመነሻ ፅሁፍ ላይ አሰተያየቶችና ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች በመቅረብ ውይይት ተደርጓል፡፡ በማስከተልም በፊደራሊዝም የሁለተኛ ድግሪ ተማሪዎች መካከል የጥያቄና ምልስ ዉድድር ተካሂዷል፡፡
በዓሉን አስመልክቶ ቀደም ሲል በተከናወኑ መርሀ- ግብሮችም በህዳር 14 ቀን 2016 ዓም በጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን ማዕከል የአልባሳት ልገሳ የተደረገ ሲሆን በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ በክረምት መርሀ ግብር በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ሥራ ተከናውኗል፡፡