በከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር የተመራ ከፍተኛ ኃላፊዎች ቡድን በኢሲሰዩ ጉብኝት አደረገ
የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር በክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የተመራና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ቡድን ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ከከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አደረጉ፡፡ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ክብርት ሚኒስትሯ በዩኒቨርሲቲው ባደረጉት ጉብኝት ወቅት በተደረገው በዚሁ ውይይት ላይም በዩኒቨርሲቲውና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መካከል ያለውን ነባር ትብብር የበለጠ ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በስፋት ተወያይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ብቸኛ የአቅም መገንቢያ ተቋም መሆኑን በማስታወስ በርካታ ሥራዎችን ያከናወነ እና ተልዕኮውምን በብቃት ሲወጣ የቆየ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በከተማ ልማት ዘርፍም ዩኒቨርሲቲው ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደ ትልቅ አጋር በመሆን የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየና አሁንም በስፋት እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን የጠቀሱት ፕ/ር ፍቅሬ አሁን ካለው የከተሞች በከፍተኛ ደረጃ የመስፋፋት ዝንባሌ ጋር ተያይዞ ከሚስተዋለው በፕላን የመመራት ችግር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያግዙ አዳዲስ የትምህርት መርሀ-ግብሮችን በመቅረጽ እና ነባር ፕሮግራሞችንም በመከለስ ሂደት ላይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር አብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደጉ በቀለ ባደረጉት አጭር ገለጻ ኮሌጁ ከምስረታው ጀምሮ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በርካታ ተማሪዎችንም በመደበኛው የትምህርት መርሀ-ግብር አሰልጥኖ ከከፍተኛ ዲፕሎማ እስከ ፒኤች ዲ ድረስ ሊያስመርቅ የቻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም በሚሰጡት የአጫጭር ጊዜ ስልጠናዎችም እና የማማከር ስራዎችም ከሁለት መቶ ሺ በላይ ለሚሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠት መቻሉንና ለተለያዩ ከተሞችም የከተማ መሪ ፕላኖችን መስራት እና የማሻሻያ ስራዎችን ከማከናወንም ባሻገር በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችም መከናወናቸውን ዶ/ር ደጉ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ደጉ በገለጻቸውም ኮሌጁ ያሉት የትምህርት ፕሮግራሞች ያሉባቸውን ክፍተቶች መለየትና ክለሳ ማድረግ፣ ከከተሜነት መስፋፋትና ዕድገት ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞችን መቅረጽ፣ በኮሌጁ ያሉትን መምህራን አቅም ማሳደግ፣ የሚሰጡት ስልጠናዎችም ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ማስቻል፣ ልዩ ልዩ ልምዶችን በመቀመር አጋርነትንና ትብብር የበለጠ ማጠናከር በወደፊት የትኩረት አቅጣጫነት ተለይተው የተያዙና በዕቅድ ተይዘው እየተሰራባቸው መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በእስካሁኑ ጉዞው በሀገር ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ያለ ተቋም መሆኑ በመግለጽ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው ከፍተኛ የከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እየመጡ ያሉ ከፍተኛ ፍላጎቶች፣ ስማርት ከተሞችን ቀድሞ የማዘጋጀትና በአግባቡ መምራት እንዲሁም በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የዩኒቨርሲቲው እገዛ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ረገድ በጋራ በምንሳራቸው ጉዳዮች መለየትና እንዴት እንደሚሰሩም መመካከር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው በዚህ ረገድም ቀጣይ ውይይቶችን ማድረግ እና ያለውን ግንኙነትም የበለጠ ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴም የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ያለቸው የካበተ ልምድና እስካሁንም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያበረከቱት አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን አስታውሰው በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲው እገዛ ለተቋሙ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በዩኒቨርሲቲው የሚገኘውን የከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ ቤተ-ሙከራን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ያሉትን የመሰረተ ልማቶቶች ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ባሉት ሥራዎችም ያለቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡