ኢሲሰዩ ለመሬት ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ጀመረ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ኢንስቲትዪት ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመጡ የከተማ ልማትና ፕላን ዘርፍ ባለሙያዎች ለአርባ አምስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡ ስልጠናውም ከሚያዝያ 17 እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከፌዴራል፣ ከክልል እና የከተማ መስተዳደር የተወጣጡ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል፡፡
በስልጠናው መክፈቻ መርሀ-ግብር ላይ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ አቶ ፈንታ ደጀን ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር እንደ የልዕቀት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ጠቅሰው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ዩኒቨርሲቲው በስፋት እያገዘ ያለ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ፈንታ አስከትለውም “ከተማን ማልማት ብዙ አቅምና ዕውቀትን ይጠይቃል፡፡በአሁኑ ወቅትም በአለም ላይ በርካታ የከተማ ልማት እና የማስፋፋት ሥራዎች በተለያየ መልኩ እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ያደጉና ለኑሮ ምቹ የሆኑ ሀገራትም በርካታ ስራዎች በዜጎቻቸው የተሰሩ ናቸው፡፡ እኛም ገና ታዳጊ ሀገር ብንሆንም እንደ አደጉት ሀገራት መስራትና ከተሞቻችንን ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ ማድረግ እንችላለን ፡፡” ብለዋል፡፡
ከተሞች ላይ የሚሰራ ስራ ውጤታማ ካልሆነ ዕድገት የሚታሰብ አለመሆኑንና በአለም ላይ ከ70 በመቶ በሀገራችንም ከ 55 እስከ 58 በመቶ የሚሆነው የጂዲፒ መጠን የሚሰበሰበው ከከተሞች መሆኑን ፣ እንዲሁም ከተሞች የተሻሉና ተመራጭ እንዲሆኑ መስራት በእጅጉ አስፈላጊ በመሆኑ እንደ ሀገር በርካታ ሰራዎችም እየተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ፈንታ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተለያዩ ስልጠናዎችን ለባለሙያዎች እየተሰጠ እና የከተማ ልማት ዋናው አንቀሳቃሽ ባለሙያው በመሆኑ የሙያተኛውን አቅም መገንባት ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ፣ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ይህን አቅም የመገንባት ስራ በግንባር ቀደምትነት እያገዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሰልጣኞችም በቆይታቸው ከመሬት አያያዝና በከተማ ፕላን ላይ ያተኮሩ ርዕሰ- ጉዳዮችን በስፋት እንደሚሰለጠኑ ገልጸው ያለውን ጥሩ አጋጣሚና የመቁጠሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም መሬትን በአግባቡ መመዝገብና ቆጥሮ መያዝ አስፈላጊ በመሆኑ፣ እንዲሁም ከተሞች የከተማ ፕላን ቢኖራቸውም በፕላናቸው መሰረት የመመራታቸው ጉዳይ አጠያያቂ በመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም ሰልጣኞች ስልጠናቸውን አጠናቀው ሲወጡ ትልቅ ኃላፊነትን በመውሰድ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ዘርፍ ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ለማ ጉዲሳ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ዩኒቨርሲተው በሀገሪቱ የነበረው ያልተማከል የፌዴራል አደረጃጀትን ተከትሎ የተፈጠረው ብቁና በቂ የሰው ኃይል እጥረት ለማሟላት በጥናት እና የሌሎች ሀገራትንም ተሞክሮ ላይ ተመስርቶ በ1987 ዓ.ም በሁለት የትምህርት ክፍሎች በዲፕሎማ ደረጃ እንዲሰጥ የተመሰረተ መሆኑን አስታውሰው ዩኒቨረሲቲው በአሁኑ ወቅት 11 መጀመሪያ ዲግሪ፣ 33 የማስተርስና 9 የፒኤች ዲ የትምህርት ፕሮግራሞችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው አንጋፋው የከተማ ልማት ኮሌጅም በርካታ ባለሙያዎችን ያፈራ መሆኑን እና በከተማ ልማት ዘርፍ ላይ ትልቅ ሚና መጫወቱን በሀገር ደረጃም ኮሌጁ እንደ ኮሌጅ ዩኒቨርሲቲውም እንደ ተቋም ለሀገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦን እያበረከቱ ያሉ ከፍተኛ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ባለሙያዎችን፣ ኃላፊዎችን፣ ሚኒስትሮችንና አመራሮችን ለማፍራት ችሏል፡፡ አሁንም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገርና ፕሮግራሞቻችንንም በመከለስ ጭምር አብረን በጥምረት እየተናበብን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ አሁን ካሉት ዘጠኝ የፒኤች ዲ ፕሮግራሞች አራቱ በከተማ ልማት ላይ ያተኮሩ ናቸው ብለዋል፡፡
በስልጠናውም ረገድ በዩኒቨርሲቲው ያሉት የስልጠና ባለሙያዎችም በርካታ ልምድና ዕውቀት ያላቸው፣ በባህሪም እጅግ ምስጉን የሆኑ አሰልጣኞች ሲሆኑ አንጋፋ ከሆኑት ዩኒቨርሰቲዎችም ተመራጭ የሆነ፣ ሰልጣኖችንም በብቃትና በባህሪም ጭምር የሚያንጽ በተግባር ላይ ያተኮረ ስልጠናን የሚሰጥ ተቋም እንደሆነ ዶ/ር ለማ ገልጸው ሰልጣኞችም በሚኖራቸው ቆይታ በሙያዊ ብቃትም ሆነ በባህርይ ታንጸው በምዘናው ላይም ፈተናውን ሙሉ በሙሉ በብቃት አልፈው ለምረቃ እንዲበቁ ያላቸውን መልካም ምኞት ገልጸዋል፡፡
በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይም ስለ ስልጠናው አጠቃላይ ሂደት እና የምዘና ሥርዓትን በተመለከተ በወ/ሮ ያልጋነሽ ጥላሁን አጭር ገለጻ የተሰጠ ሲሆን በሰልጣኞችም በስልጠናውና በምዘናው ሂደት ላይ ለተነሱ ጥያቆዎችና አስተያየተቶች በዶ/ር አዜብ አሰፋ የስልጠና ኢንስቲትዩት ዲን እና በወ/ሮ ዚነት ኢብራሂም የከተሞች ገቢ ሪፎርም ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ ለጥያቄዎቹ ምላሽና ማብራርያ ተሰጥተዋል፡፡