ኢሲሰዩ በተለያዩ የትምህርት መርሀ-ግብሮች ያሰለጠናቸውን 2216 ተማሪዎችን አስመረቀ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ2016 ዓ.ም በተለያዩ መርሀ-ግብሮች ያሰለጠናቸውን 2216 ተማሪዎችን ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ዋና ጊቢ በድምቀት አስመረቀ፡፡ ተመራቂዎቹም 122 በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 2119 በሁለተኛ ዲግሪ እና 27 ደግሞ በፒኤች ዲ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ተመስገን ቡርቃ የዴሞክራሲ ማዕከል ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ምስረታ፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ጉዞና ከፌዴራሊዝም ስርዓት አጀማመር ጋር ጠንካራ ቁርጠኝት ያለው መሆኑን፣ ዩኒቨርሲቲው ከምስረታው ጀምሮ ባለው ጉዞው ከሰባ ሺህ በላይ ምሩቃንን በማፍራት እና ምሩቃኑም በከፍተኛ የመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተሰማርተው መንግስትና ሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነቶች እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አስከትለውም የሲቪል ሰርቪሱ ያሉበትን መሰረታዊ ስብራቶች ለመጠገንና ዘመናዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት መንግስት የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ተመስገን ቡርቃ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ሰርቪሱን አቅም የመገንባት ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ ይህን ተልዕኮውን ለመወጣት በትጋት እየሰራ ያለ ስለሆነ፣ ተቋማዊና አስተዳደራዊ መዋቅር የሚያስፈልገው መሆኑን በማመንና፣ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ዕቅድን መሰረት ያደረገ የሽግግር ሥራዎችን እያሰራ እንደሚገኝ አመልክተው፣ የስራ አመራር ቦርዶም ይህ ጉዞ እንዲሳካ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ለዕለቱ ተመራቂዎችም ባስተላለፉት መልዕክት፣ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ቆይታ ያካበቱትን ዕውቀትና ክህሎት በሚሰማሩበት የስራ መስክ ሀገሪቷንና ኅብረተሰቡን በታማኝነትና በታታሪነት፣ ከአድልኦና ከሙስና በጸዳ፣ ሰብዐዊነትን በተላበሰ መልኩ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲቃለል የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ በብርቱ ጥረትና ትጋት በየትምህርት ፕሮግራሞቹ የተቀመጡትን መስፈርቶች በሚገባ በማጠናቀቅ ህልማችሁን ዕውን ለማድረግ በመቻላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ በማስከተልም፣ ዩኒቨርሲቲው በእስካሁኑ ጉዞው ከ70 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ከዲፕሎማ እስከ ፒኤች ዲ ዲግሪ ድረስ አስተምሮ ማስመረቅ የቻለ መሆኑንና ከእነዚህም መካከል 700 የሚሆኑት የጎረቤት ሀገራት ፐብሊክ ሰርቫንቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህም ለሀገራችን ኩራት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ሚኒስቴር ስር እንዲደራጅ በመንግስት በመወሰኑ እና በሀገራችን ካሉት የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በድህረ ምረቃና ምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ምድብ መመደብ መቻሉ፣ የሀገራችንን ሲቪል ሰርቪስ አቅምና ብቃት የመገንባት ተልዕኮውን ለመወጣት ጠንካራ መንፈስና ተነሳሽነት የፈጠረለት መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ፍቅሬ በ2016 ዓ.ም ከመንግስት በተመደበው 837 ሚሊዮን ብርና ከባለድርሻ አካላት በተገኘ ድጋፍ በርካታ የትምህርት፣ የምርምርና ማማከር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች የተከናወኑ እና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችም ለመንግስት ሰራተኞች የተሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳዳሪነቱና ተመራጭነቱ እያደገ በመምጣቱም በ2016 ዓ.ም 7268 ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር የቆየ ሲሆን፣ ለ2017 የትምህርት ዘመን ወደ 7000 የሚጠጉ የማስተርስና የፒኤችዲ ተወዳዳሪዎችን በመለየት ብሔራዊ የድህረ-ምረቃ መግቢያ ፈተና እንዲወስዱ ዝርዝራቸው ለትምህርት ሚኒስቴር መላኩን አመልክተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ፍቅሬ በንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው ብቁና በቂ የአካዳሚክ ሰራተኞች እንዲኖሩት በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አብራርተው 31 አዳዲስ የትምርት ፕሮግራሞችም ቀረጻ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ የፐብሊክ ሴክተሩን አቅም ከመገንባት አኳያም በ2016 ዓ.ም ከ3206 በላይ ስልጠናና የምዘና ስራ መከናወኑንም አክለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት ሶስት አሰርት ዓመታት የሀገራችንን ሲቪል ሰርቪስ የሰው ኃይል በማልማትና በመንግስት የተዘረጉ የሪፎርም ፕሮግራሞችን ትግበራ በማማከር፣ ሴክተሩ ለሀገር ግንባታ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በምርምር ሥራዎች ላይ በሚያደርገው ትኩረት በማሳደግ በ2016 ዓ.ም በ5 ሚሊዮን ብር በጀት 49 ምርምሮችን ያካሄደ ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ተከታታይ አመታት በአጠቃላይ 497 ችግር ፈቺና ለፖሊሲ ግብዐት የሚሆኑ ምርምሮች መሰራታቸውንም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተሟላ ራስ ገዥ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን በመንግስት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ የሽግግር ዕቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የገለጹት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፣ ትምህርትና ስኬት የህይወት ዘመን ጉዞ አካል ቀጣይ በመሆናቸው፣ በቀጣዩ የሥራ ዓለም ተመራቂዎች የበለጠ አቅማቸውን በመገንባት ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት በሙሉ ኃየላቸው መደገፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡