ኢሲሰዩ ባለ ስምንት ወለል አዲስ ህንጻ ለማስገንባት ውል ተፈራረመ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ለሚያሰራው ባለ ስምንት ወለል ህንጻ ፕሮጀክት ባወጣው ጨረታ መሰረት የጨረታው አሸናፊ ከሆነው ጉተማ ፈሬሳ ኮንስትራክሽን ጋር መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም የግንባታ ማስጀመርያ ስምምነት ውል ተፈራረመ፡፡
በስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅትም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ እንደገለጹት ይህ አዲስ የሚገነባው ባለስምንት ወለል ህንጻ በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ሊባል የሚችል እስካሁን ካከናወናቸዉ ፕሮጀክቶች ትልቁ ፕሮጀክት ሲሆን በተለይ ተቋሙ ራስ ገዝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደአንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሊይዛቸዉ የሚገቡ ዘመናዊ መማሪያ ክፍሎች ዘመኑ የደረሰባቸዉ ቴክኖሎጂዎች አደራጅቶ ይይዛል ብለዋል፡፡ ህንጻዉ ሲጠናቀቅ በርካታ አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ ክፍሎች ለተለያየ አገልግሎት የሚዉሉ ዘመኑ ባፈራቸዉ ቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ የዉስጥ ቁሳቁሶች አብሮ ያካተተ ሲሆን ለዩኒቨርስቲያችንም እንደ አንድ ''ላንድ ማርክ'' ተደርጎ የሚወሰድ ነዉ ብለዋል፡፡ ተቋራጩም ባለው የካበተ ልምድ እና ቀደም ሲልም በዩኒቨርሲቲው ሌሎች ህንጻዎችንም በገባው ውል መሰረት አጠናቆ ያስረከበ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ይህን ፕሮጀክትም በውሉ መሰረት አጠናቆ እንደሚያስረክብ ሙሉ እምነት እንዳላቸዉ በመግለጽ ፤ነገር ግን በተቻለ መጠን በተቀመጠዉ ግዜ ሰሌዳ አጠናቆ ለአገልግሎት እንዲደርስ፣ ተቋሙ የጀመረዉ የራስ ገዝ ሂደት የሚያፋጥን ስለሚሆን አደራ እያልን ድርጅቱም ሀገራዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
የጉተማ ፈሬሳ ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉተማ ፈሬሳ በስምምነቱ የተሰማቸው ደስታ ገልጸው ፕሮጀክቱን በውሉ መሰረት በማጠናቀቅ ለዩኒቨርሲቲው ለማስረከብ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸው ከዩኒቨርሲቲውና ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር በመነጋገር፣ በመወያየትና በመተጋገዝ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንደሚሆን ቃል ገብተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ አማካሪ ኡቦን ቮያጅ አማካሪ ድርጅት ሀላፊ አቶ አለሙ መረራ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ሁሉን አካታችና ዘመናዊ ህንጻ ከመሆኑ እና ስምምነቱም ህንጻውን ከነሙሉ ግብዐቱ አጠናቆ ማስረከብን የሚያካትት በመሆኑ ከተለመደው የግንባታ አካሄድ ወጣ ያለ መሆኑን ተገንዝቦ አሸናፊዉ ድርጅት ከወዲሁ በሁሉም ረገድ ብቁ ሆኖ መገኘት ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል፡፡
የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ሂደት በተመለከት የኢሲሰዩ የምህንድስናና ጥገና አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለሙ ሲሳይ እንደገለጹት ይህ ሁለገብ የመማርያ ህንጻ ለመገንባት ግልጽ ጨረታ የወጣ ሲሆን የተለያዩ ተወዳዳሪዎች ተወዳድረዉ 5 ተወዳዳሪዎች የተቀመጠዉን መስፈርት ያሟሉ ሲሆን ከእነዚህ ዉስጥም የጉተማ ፈሬሳ ኮንስትራክሽን ድርጅት በ 2,326,162,955.48 (ሁለት ቢሊየን ሶስት መቶ ሀያ ስድስት ሚሊየን አንድ መቶ ስልሳ ሁለት ሺ ዘጠኝ መቶ አምሳ አምስት ብር ) እንዳሸነፈ አብራርተዋል፡፡
የሚገነባው ሕንጻም እጅግ ዘመናዊ መሆኑ የጠቀሱት አቶ አለሙ በውስጡም 19 የተለያዩ ቢሮዎችን፣ 24 አንድ መቶ ተማሪዎችን የሚይዙ የመማሪያ ክፍሎችን፣ 18 ሰላሳ ሰዎችን የሚይዙ ስማርት ክፍሎችን፣ 285 እና 110 ሰዎችን የሚይዙ ሁለት አዳራሾችን ፣ 11 ሱቆችን፣ 1 ሺ ተማሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ አንድ ቤተ-መጽሐፍ፣ 6 ተማሪዎች እርስ በርስ የሚወያዩባቸው ስቱደንት ኮርነርስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ ፣ መኪናዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚያስችል የመኪና ማቆሚያና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጥ ህንጻ መሆኑን ገልጸዋል፡