ኢሲሰዩ ከትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አደረገ
የኢትዮጲያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስትር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከዩኒቨርስቲዉ ማህበረሰብ ጋር ህዳር 20 ቀን 2014 ዓ.ም በዩኒቨርስቲዉ ሕዳሴ አዳራሽ የትዉዉቅና ዩኒቨርሲቲው ወደፊት ሊከተለው የሚገባውን ተቋማዊ እንቅስቃሴ አስመልከቶ ዉይይት አድርገዋል፡፡
በዉይይቱ ላይም የኢሲሰዩ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ለክቡር ሚኒስትሩና ለከፍተኛ የስራ ኃላፊዎቹ የዩንቨርስቲዉ አመሰራረት ፣የተቋቋመበት አላማና ተልዕኮ በተመለከተ ገለጻ ያደረጉላቸው ሲሆን ዩንቨርስቲዉ የአቅም ግንባታ ተልእኮዉን ለመወጣት ባለፉት 27 አመታት በዋናነት በትምህርት፣በስልጠና ናማማከር ፣በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ያከናወናቸዉን አበይት ተግባርት በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ በማስከተል ተቋሙ ባለፉት 5 አመታት ዉስጥ ለሁሉም የፐብሊክ ሴክተር ሰራተኞች በእኩልነት የሚያገለግል ተቋም ለማድረግ የሚሰጠዉን አገልግሎት በፍታዊነት መርህ ተደራሽ እንዲሆን የተማሪዎች ምልመላ ፣መረጣና የቅበላ ፖሊሲዉን ፕሮቶኮል እንዲቀየር በመደረጉ ሁሉም የመንግስት ሰራተኛ ወደ ዩኒቨርስቲዉ ገብቶ ለመማራ የተቀመጠዉን ጠንካራ የመግቢያ መስፈርት ማሟላት ብቻ የሚጠበቅበት ሥርዓት መዘርጋቱን አመልክተው ይህም በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ተመራጭ ዩኒቨርስቲ ወደ መሆን ተሸጋግሮአል ብለዋል ፡፡
በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲዉ ከተጠሪነት ለዉጥ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ግዜ አንዳንድ አደረጃጀትና የዉስጥ አሰራር ከዩኒቨርስቲዉ ተልዕኮ ጋር በማጣጣም የማደራጀት ስራ እንደተጀመርና የፐብሊክ ሴክተሩም ዘርፍ ስር ነቀል ለዉጥ ለማምጣት ትልልቅ ፕሮጀክቶች መጀመራቸዉን፤ ይህም በቀጣይነት እንደሚሰራ በመግለጽ ለዚህም ዓላማ መሳካትም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ የወደፊት ተጨማሪ የትኩረት አቅጣጫዎች በዚህ ዉይይት እንዲቀመጡ በመግለጽ ንግግራቸዉን አጠናቀዋል፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የዩኒቨርሲቲው ተጠሪነት ለትምህርት ሚኒስቴር መሆኑን ተከትሎ እንኳን ወደ ትምህርት ሚኒስቴር በደህና መጣችሁ በማለት ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በመተዋወቃቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ አስከትለውም ከትምህርት ተቋማት እና በትምህርት ዘርፉ ካሉ ተጠሪ ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ባለፉት 40 ዓመታት በሀገራችን ለደረሰው የትምህርት ጥራት ውድቀት አራት መሰረታዊ ችግሮችን ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ ችግሮችም በዘርፉ የሚታየው አጠቃለይ የሆነ የብቃት ችግር፣ መሰረታዊ የሆነ የሞራል ክስረት፣የትምህርትና ፖለቲካ አብሮ መዛመድ እና ከክልላዊነት ጋር የተያያዙ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰው እነዚህን ችግሮች በማረም ለተሻለ ስራ በእኔነት ስሜት መነሳት እና የትምህርት ሥርዓቱን መለወጥ አስፈላጊ ነዉ ብለዋል ፡፡ ለዚህም በትምህርት ስርዓቱ ያለውን የትምህርት ጥራት መሰረታዊ ችግሮችን ከፖለቲካ አስተሳሰብ በማላቀቅና ለመፍትሔው ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አበክረዉ ተናግረዋል ፡፡ በተጨማሪም ለችግሮቹ መፍትሄ ናቸው ብለው ያሉዋቸውን ዋና ዋና ነጥቦች እስቀምጠዋል፡፡
የኢትዮጲያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲም በተለይ አሁን የሚታዩ አንዳንድ የውስጥ አሰራሮችን ከመለወጥና ከተሰጠዉ ተልእኮ አንጻር ትልቅ ስራ እንደሚጠበቅበት በመግለጽ በዩኒቨርሲቲውን የወደፊት ትኩረት አቅጣጫ ላይ ማህበረሰቡ በጥልቀት በመነጋገርና ግልጥ የሆነ አቅጣጫን በማስቀመጥ መንቀሳቀስ ብሎም የሀገሪቱን የሲቪል ሰርቪስ ሴክተር ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት መስራት እንደሚገባው በማመላከት ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ሙሉ በሙሉ ተቋሙን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ለዚህም እያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በኃላፊነትና በእኔነት ስሜት ጊዜ ሳያጠፋ በአገራችን የፐብሊክ ሴክተር ላይ ለውጥ እንዲመጣ የራሱን አሻራ ማስቀመጥ እንዳለበት እና በትጋት በመስራት ልዩ አስተዋፅኦ ማበርከት ከዩኒቨርሲቲው እንደሚጠበቅ አሳስበዋል ፡፡
በመጨረሻም የየትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ለዩኒቨርሲቲው የትምህርት ሚኒስቴር ትክክለኛ ሥፍራው መሆኑን ጠቁመው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚነሱት አንድንድ ተግዳሮቶች በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ብቻ የሚገኙ ችግሮች ሳይሆኑ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲዎች ችግር መሆኑን በመገንዘብ ዩኒቨርሲቲው ማስተካከል የሚገባውን የውስጥ ሥራ በራሱ በማስተካከል ለታላቅ ሀገራዊ እና ተቋማዊ ተልዕኮ ስኬት መነሳት እንዳለበት በማመላከት ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጎኑ አንደሚሆን ዶ/ር ሳሙኤል አለምክተዋል፡፡