ኢሲሰዩ ካውንስል የ2016 የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን ግምገማ አካሄደ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የዩኒቨርሲቲውን የ2016 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የስራ ክንውን እና መደበኛ የሪፎርም ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ አካሄደ፡፡
በግምገማ መድረኩ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር መድረኩ ያለፉት ዘጠኝ ወራት በሪፎርምና በዕቅድ የተያዙ ሥራዎች ክንውን የሚገመገምበት እና በቀጣይ ለሚተገበሩ ሥራዎችም አቅጣጫ የምናስቀምጥበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ከ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት ጀምሮ የተሟላ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆንና የተሸለ መዋቅራዊ፣ አስተዳደራዊና አካዳሚያዊ ነጻነትን ሊያጎናጽፈን የሚችለውን ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆንን የሚያስችል የዝግጅት ጊዜ ዕቅድ አቅደን እየሰራን የቆየን በመሆኑ በዚህ ረገድ የተሰሩ ሥራዎችን በዝርዝር የምንገመግምበት፤ አጀንዳዎቹም ሰፋፊና በርካታ ጉዳዮችን ያካተቱ በመሆናቸው እየተተገበሩ ያሉትን ሥራዎች ከምን ላይ እንደደረሱ ካዉንስሉ የሚያረጋግጥበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የምርምር ዩኒቨርሲቲ መሆን እና ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆን እራሳቸውን የቻሉ ሁለት የተለያዩ አጀንዳዎች መሆናቸው የገለጹት ፕ/ር ፍቅሬ በምርምር ዪኒቨርሲቲነት የተቀመጡትን ሀገራዊ መስፈርቶች በሚገባ ማሟላት ወሳኝ መሆኑን ፣ ራስ-ገዝ ዩኒቨርቲነትም የሚፈለገውን መስፈርት ተሟልቶ ሲገኝ ብቻ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራትን ከእነዚህ መስፈርቶች አኳያ በስፋት እንገመግማለን ብለዋል፡፡
እነዚህን አጀንዳዎች ለመተግበርም ለዩኒቨርሲቲው በተፈቀደው የምርምር ዩኒቨርሲቲ መዋቅር መሰረት የሰራተኞች ምደባ መደረጉ ትልቁን መደላድል የፈጠረ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጣው ለውጥ ምን እንደሆነ፣ ለተልዕኮ ስኬት እጅግም ረብ የማይኖራቸውን ለማጥራት በቀጣይ የሚሰራበት ጉዳይ መሆኑን ያወሱት ፕ/ር ፍቅሬ በስፋት አዲስ ከተተገበረው መዋቅር ጋር ተያይዞ የሴኔት መተዳደሪያና የተከታታይ ትምህርት መመሪያ ብቻ የተሸሻሉ በመሆናቸው በቀጣይ ሌሎች በርካታ መሻሻል ያለባቸው ደንቦች ፣ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች መታየት እንደሚኖርባቸው በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡
ራስ-ገዝ መሆንን አስመልክቶም ራስ ገዝነት ‘'ራስን በራስ ማስተዳደር’’ ማለት ሳይሆን ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የፋይናንስ አቅም ማሳደግ የተለያዩ የገቢ ምንጮቹን በመለየት ወደ ትግበራ በመግባት ገቢ ማመንጨት፣ ተያያዥ የአፈጻጸም ነጻነቶች ማግኘት ነዉ ብለዋል፡፡ራስን በራስ ማስተዳደር ያለበቂ ሀብት የማይታሰብ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እንዲኖረው ለማስቻል 22 የተጠኑ የገቢ ማመንጫ ተለይተው እየተሰራባቸው መሆኑን፣ እና ሌሎችም በማጠናከር በ2020 ዓ.ም 30 በመቶ የራሳቸውን በጀት ከውስጥ ገቢ ለመሸፈን የተጣለውን ግብ ለማሳካት መትጋት ያስፈልጋል ፡፡ ሌላው ብቁና በቂ የሰው ኃይል መኖር፣ ያሉት የትምህርትና የስልጠና ፕሮግራሞች ተፈላጊነት፣ የተማሪዎች ምልመላና ቅበላ ፖሊሲዎች፣ የትምህርትና ስልጠና ጥራትን ማስቀጠል፣ ጠንካራ የምርምርና የማማከር ስርዓትን መፍጠር፣ በድህረ ምረቃ የሚሰራ የምርምር ውጤት በአግባቡ ማደራጀት፣ የዲጂታል የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ማጠናከር፣ በትብብርና ትስስር እንዲሁም ዓለማቀፋዊነት አንጻር እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም እና ውጤቶች፣ ደረጃውን የጠበቀ የመሰረተ ልማት እና ፋሲሊቲ ማስፋፋት እና ሌሎች አንኳር ጉዳዮች ላይ የተሰሩና የታዩ ጉድለቶችን በማንሳት መወያየት እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት በኦዲት ግኝት ያልተገኘበት ተቋም መሆኑን አስገንዝበው ይህ ጠንካራ የኦዲት ስርዓት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ለካውንስሉ ገልጸው የበጀት እጥረት፣ ለተማሪዎች በሚቀርበው የምግብ አቅርቦት እና ሌሎችም ውጫዊ ጉዳዮች ጫና የፈጠሩበት መሆኑን ለካውንስሉ ገልጸዋል፡፡
በማስከተልም በአራቱ ዘርፍ ማለትም በአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ፣በምርምርና ትብብር ዘርፍ ም/ፕሬዚዳንት፣በማናጅመንት ዘረፍ እና በአስተዳደር እና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዘርፍ የተከናወኑ የየዘርፋቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን እና የሪፎርም ሥራዎች ሪፖርት ለካውንስሉ ያቀረቡ ሲሆን ከቀረበው ሪፖርት መሰረትም የሪፎርም ስራዎችን በተመለከተ ከራስገዝነት ተልዕኮ ልየታ፣ በመረጃ አያያዝና ዲጂታል ሥርዓት ግንባታን በተመለከተ IFMIS፣ ICSMIS፣ EGP፣የCCTV ካሜራና የሠራተኞች ቁጥጥር በጣት አሻራ ቴክኖሎጂዎች ማካሄድ መቻሉን ፣ አዳዲስ የካሪኩለም ማሻሻያዎች፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ እና የሰው ኃይልንም በበቂ ሁኔታ ለማብቃት የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውና ስልጠናዎች መሰጠታቸው በሪፖርት ቀርቧል፡፡ የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ደንቦች መከለሳቸው፣ የሚሰሩ የምርምር ጭብጦች የተለዩ መሆናቸው፣ የተጀመሩ አጋርነቶችን ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድጉ መደራጀታቸው በተለይ ዩኒቨርሲቲው የጎረቤት ሀገራትን ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ ለመደገፍ እና ትብብርን ለማጠናከር እየሰራ ያለዉ ስራ በዝርዝር የቀረበ ሲሆን የዓለም አቀፍ ተማሪዎችና መምህራን በተቋሙ ተሳትፎአቸዉ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ማለት እንደለበት ተመላክቷል ፤ በ 2015 ዓ.ም ፋይናንስ ከተደረጉ ምርምር ስራዎች አስራ ሁለቱ መታተማቸው ከ2011 እስከ 2015 ዓ.ም የተካሄዱ አመታዊ የምርምር ጉባኤዎች ላይ የቀረቡ የጥናት ወረቀቶች በተቋሙ ድረ ገጽ ላይ መጫናቸው እና በማማከር አገልግሎትም ጥራትና ብዛትን ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸው በሪፖርቶቹ ተመላክተዋል፡፡
አስተዳደርና ልማትን በተመለከተም ዩኒቨርሲቲው ባካሄደው ሰራተኞች ምደባ ለ 979 ሰራተኞችን በአዲሱ መዋቅር መሰረት ሁሉም ሰራተኞች በሚባል ደረጃ በአሁኑ ወቅት ላይ ምደባ ማግኘታቸው ተገልጸዋል፡፡ የበጀት፣ የፋይናንስ፣ የግዥና የንብረት አስተዳደርን አስመልክቶም በርካታ ስራዎች መከናወናቸው በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 37,108,671.57 ብር ከወጪ ቀሪ የውስጥ ገቢ መገኘቱ፣ አጠቃላይ የበጀት አጠቃቀሙም 82.25 በመቶ መሆኑ እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ መሰረተ ልማትና ፋሲሊቲዎች ማደረጃትን በተመለከተ በአዲስ አበባ ዋናው ግቢ በተለይ ትምህርትና ስልጠናን በዘመናዊ መንገድ የሚያስኬዱ G+7 የስልጠና ማዕከል እና G+8 ሁለገብ ሕንጻዎች ግንባታ እያካሄደ መሆኑን በተጨማሪም ነባር የወሊሶ ካምፓስ ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በ2015 መጨረሻ ተግባራዊ ለተደረገዉ የመጀመሪያ ዲግሪ የመዉጫ ፈተና (Exit Exam) ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በኢሲሰዩ ዉስጥ የተዘጋጀ ሲሆን ተገቢዉን ግብዓት በማቅረብና በማስተባበር እንዲሁም የሌሎች ተቋማት ተማሪዎች ጭምር በዩኒቨርሲቲዉ እንዲፈተኑ በማመቻቸት ረገድ ዩኒቨርሲቲዉ ተቋማዊ ሀላፊነቱን በብቃት በመወጣት ጉልህ ሚና እንደተጫወተ ተገልጿል፡፡
የካውንስሉ አባላትም በቀረበው ሪፖርት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች፣ ሀሳብና አስተያየቶችን እንዲሁም መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮችን በማንሳት ሰፊ ውይይቶችን ሲያደረጉ አባላቱ ላቀረቧቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶችም የየዘረፉ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማጠቃላያዉም ላይ ፕሬዚዳንቱ እንዳሳሰቡት በተለይ እንዲህ አይነት ግምገማ እነደ አመራርም ትልቅ ትኩረት የምንሰጠዉ ፣ የካዉንስል አባላትም በግልጽነት ጥያቄዎች እና ማብራሪያዎች የሚያነሱበት እና የምንወያይበት መድረክ እንደመሆኑ የካዉንስል አባላት በስብሰባ በመገኘት ሀላፊነታቸዉን መወጣት አለባቸዉ ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ለአራተኛ ሩብ አመት አቅጣጫ በማስቀመጥ የዕለቱ ግምገማ ተጠናቋል፡፡