ኢሲሰዩ ካውንስል የ2016 ግማሽ ዓመት ግምገማ አካሄደ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የዩኒቨርሲቲውን የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የሪፎርም ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ አካሄደ፡፡
በግምገማ መድረኩ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር መድረኩ በመደበኛ እና በሪፎርም ስራዎች ላይ የተከናወኑ ስራዎች ግምገማ የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ካውንስሉ በመጀመሪያው የሩብ ዓመት ግምገማ ላይ በቀጣይ ሊተኮርባቸው የሚገቡ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን አስታውሰው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ሚኒስቴር የድህረ ምረቃና የምርምር ዩኒቨርሲቲ ምድብ ውስጥ ከመመደቡ ጋር ተያይዞ ብቃት ያለው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ለመገኘት በትምህርት ሚኒስቴር ከተቀመጡት መስፈርቶች መካከል ምንም እንኳን በአካዳሚክ ተመራማሪዎች ብዛት፣ በጀትና የድረ ምረቃ ትምህርት መርሀ-ግብሮች ላይ ጥሩ ቁመና ቢኖረውም ፤ አለማቀፋዊና ሀገር ውስጥም ከሚገኙ ተቋማት ጋር ጠንካራ ትስስርና ጉድኝት የሌለ መሆኑ፣ ደረጃውን የጠበቀ ለምርምር የሚውል ግብዐትና ፋሲሊቲ አለመሟላት በዩኒቨርሲቲው የሚታዩ ጉድለቶች መሆናቸውን በመውሰድ፤ በእነዚህ ጉድለቶች ላይ ስራዎች በዕቅድ ተይዘው ሊሰሩ እንደሚገባ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የተሰሩ ስራዎችን ይገመገማሉ ብለዋል፡፡
ሌላው ዩኒቨርሲቱው በቀጣይ ራስ -ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በሚያደርገው ጉዞ ባለው የሽግግር ጊዜ ተሰርተው ሊጠናቀቁ ይገባል ተብለው የተለዩ ስራዎች ማለትም ራስ ገዝነት ያለ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም የሚታሰብ ባለመሆኑ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እንዲኖር ማስቻል ፣ የትምህርት ፕሮግራሞችን በፐብሊክ ሴክተሩም ሆነ በሀገር ደረጃ ተመራጭና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የምርምር ስራዎችን በጠንካራ አስተዳደራዊ ስርዓት ሊመሩ የሚገባቸው መሆኑ እንዲሁም አዲስ በተዘጋጀው መዋቅር መሰረት የምርምር ዩኒቨርሲቲ አደረጃጀትን ተከትሎ ሰራተኞችን በተገቢው ቦታ በመደልደል ዕድቆችን በአግባቡ ታቅደው ወደስራ እንዲገባ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ግምገማው የሚደረግ መሆኑን ለካውንስሉ ገልጸዋል፡፡
በግምገማ መድረኩም የአካዳሚክ ጉዳዮች ዘርፍ፣ የምርምርና ትብብር ዘርፍ፣ የአስተዳደርና ልማት ዘርፍ እንዲሁም የማናጅመንት ድጋፍ ዘርፍ የስድስት ወራ የአፈጻጸም ሪፖርት በዶ/ር ለማ ጉዲሳ፣ በዶ/ር አለማየሁ ደበበ፣ በዶ/ር ታዴዎስ ሜንታ እና በዶ/ር አብርሃም ሀጎስ ቀርቧል፡፡
ከመማር ማስተማር ሂደቱ ጋር ተያይዞ በቀረበው ሪፖርት ዘርፉ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በ2016 በጀት ዓመት ሊሰሩ የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም መሰረት የትምህርት ፕሮግራሞች እና የስርዓተ -ትምህርት ክለሳ የተደረ ሲሆን የሪፎርም አጀንዳዎቹንም በእቅድ ውስጥ በማስገባት በትኩረት እየተሳራባቸው መሆኑ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የሴኔት ሌጅስሌሽን ማሻሻያ፣የአካዳሚክ ሰራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና አጋርነት፣ ትስስርና ዓለማቀፋዊነትን ከማሳደግ አኳያ ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ በምርምርና ትብብር ዘርፍ በቀረበው ሪፖርትም ዘርፉ የለውጥ አጀንዳዎችን ለይቶ በልዩ ትኩረት እየሰራባቸው ሲሆን የምርምር ስራዎችን ብዛት ፣ ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ ባደረገው ጥረት 67 የምርምር ስራዎችን ለማሳተም ከዩኒቨርሲቲው ጆርናሎች ጋር የማያያዝ ሥራ ተሰርቷል፤ 58 የምርምር ስራዎችም ፋይናንስ ተደርገዋል፡፡ የማማከር አገልግሎቶችም በብዛትና በጥራ ከመስጠት፣ የተመራማሪዎችን አቅም ከማሳደግ ፣ የማህበረሰብ ተሳትፎ እና የኢንዱስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማሳደግ አኳያ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸው በሪፖረቱ ቀርቧል፡፡
የአስተዳደርና ልማት ዘርፍ እንዲሁም የማናጅመንት ድጋፍ ዘርፍም ስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለካውንስሉ ያቀረቡ ሲሆን በቀረበው ሪፖርትም 894 ሰራተኞች በአዲሱ መዋቅር መሰረት ተደልድለው ቦታ ማግኘታቸው፣ምቹ የስራ አካባቢ ለመፍጠር እና ግብዐቶችን የማሟላትና ለየሥራ ክፍሎች የማሰራጨት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ተማሪዎችም one card ሲስተምን እንዲጠቀሙ ተደርጓል፡፡ በጀትን በተመለከተም 35 ሚሊዮን ብር ገቢ የተገኘ መሆኑንና ከአጠቃላይ በጀትም 66.36 በመቶውን ዩኒቨርሲቲው መጠቀሙ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ የሪፎርም ስራዎችን በተገቢው ሁኔታ ለማስኬድ ያስችል ዘንድ የሪፎርም አስፈጻሚ ግብረ-ሀይል በየዘርፎች በማደራጀት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑም ለካውንስሉ ከቀረበው ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡
የካውንስሉ አባላትም በቀረበው ሪፖርት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች፣ ሀሳብና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን የየዘረፉ ኃላፊዎች በተነሱት ጥያቄች እና አስተያየቶች ላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማጠቃላያዉም ላይ ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ እንዳሳሰቡት በተለይ እንዲህ አይነት ግምገማ እነደ አመራርም ትልቅ ትኩረት የምንሰጠዉ ፣ የካዉንስል አባላትም በግልጽነት ጥያቄዎች እና ማብራሪያዎች የሚያነሱበት እና የምንወያይበት መድረክ በመሆኑ የካዉንስል አባላት እንዲህ አይነት ግምገማ ባህል እንዲያደረጉ አሳስባለሁ ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ለሶስተኛ ሩብ አመት አቅጣጫ በማስቀመጥ የእለቱ ግምገማ ተጠናቋል፡፡