ኢሲሰዩ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የምርምር አስተችቶት አውደጥናት አካሄደ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የሁለት ቀናት የምርምር አስተችቶት አውደ-ጥናት ከጥር 23-24 /2015 ዓ.ም በአባይ አዳራሽ አካሄደ፡፡ በአውደ ጥናቱ ላይም የተለያዩ የፌዴራል ፣ የክልልና የሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የሴክተር መስሪያ ቤት ሀላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
ዶ/ር ተመስገን ቡርቃ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ በአውደ ጥናቱ መክፍቻ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ዩኒቨርሲቲዎች በተሰጣቸው የማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ተልዕኮ የሚያከናውኗቸው ተግባራት የሀገሪቱን ችግር የሚፈቱ መሆን እንዳለባቸው በመጠቆም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲም ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት በትምህርት በስልጠናና የማማከር አገልግሎት እንዲሁም በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችም ሲያከናውን መቆየቱን አመልክተዋለ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዩኒቨርሲቲ ስር የተመደበ በመሆኑ ይህን ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ማከናወኑን የበለጠ አስጠብቆ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ የምትገኝ መሆኗን ያወሱት ዶ/ር ተመስገን ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዱ የሙስና መንሰራፋት እንደሆነ ጠቁመው ዜጎች መብቶቻቸውን እና አገልግሎትን በገንዘብ ሊገዙ የሚገደዱባቸው እውነቶች መኖራቸው ጠቁመዋል፡፡ ሙሰኝነት መንግስት ሙሉ አቅሙን በልማትና በሀገር ግንባታ ላይ እንዳያደርግ ችግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ይህ ችግር የሚፈታው ከመንግስት ቁርጠኝነት በተጨማሪ የመላው ህብረተሰብ ተሳትፎ ሲታከልበት ነው፡፡ ንቅዘት በሀገራችን አጠቃላይ ዕድገት ላይ እያደረሰ ያለው ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር በሀገር ሰላምና በዜጎች ህይወት ላይ ያለው ጫናም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህን አደጋ ለመቀልበስ ሳይንሳዊ የሆነ ጥናትና ምርምር መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ምሁራንም ጥረት ማድረግ ይጠብቅባቸዋል፡፡ በመሆኑም የዛሬው መድረክ ዓላማና ግብ ንቅዘትን ከየአቅጣጫው በመመርምርና በመተንተን መገለጫዎችን ብቻ ሳይሆን ምክንያቶችንም ጭምር ማሳየት እና የመፍትሄ አቅጣጫንም የሚያመላክት ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ያለው ስራ አበረታች ቢሆንም የበለጠ አጠናክሮ መሄድ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውንና በጥናቱ ሂደት የተሳተፉትን አካላትም አመስግነዋል፡፡
ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት በበኩላቸው ለአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ዩኒቨርሲቲው እንደማንኛውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የትምህርት ፣ የስልጠናና ማማከር አገልግሎት እንዲሁም የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ቢሆንም በዋናነት የሲቪል ሰርቪሱን ሰራተኞች በመቀበል የሚያሰለጥን መሆኑ ከሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተለየ ያደርገዋል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም ከሃምሳ ሺህ በላይ ምሩቃንን ያፈራ እና እነዚህም ምሩቃን በሀገሪቱ የፌዴራልና የክልል ተቋማት እንዲሁም የከተማ መስተዳድሮች ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦን ያበረከቱ እና በማበርከት ላይ የሚገኙ ምሩቃንን አፍርቷል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባለው የሃያ ስምንት ዓመታት ዕድሜ ተጠሪነቱ ለተለያዩ ተቋማት ሲቀያየር የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በተደረገው አዲስ አደረጃጀት በኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ስር መካተቱን የጠቀሱት ፕ/ር ፍቅሬ ዩኒቨርሲቲው አሁን ባለው ቁመናና ደረጃ አንጻር ከቀደምት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በምርምር ዩኒቨርሲቲነት መመደቡንና በማህበረሰቡ ዘንድም ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው በመንግስት መስረያ ቤቶች ላይ በመሆኑ የምርምር የትኩረት መስኮቹም የሚነሱት ከመንግስት ነው፡፡ መንግስትም ሃላፊነቶችም የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላትና የሰላምና ደህንነት ፍትህን ማስከበር በመሆኑ የምርምር ስራዎቻችን በእነዚህና መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በምርምር ስራዎቻችንም በርካታ ሥራዎች የተሰሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ፕ/ር ፍቅሬ በከተሞች ልማት፣ ሰላም፣ ፍትህ እናሌሎች ልዩ ልዩ ስራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሙስናና የመልካም አሰተዳደር ችግሮች ላይ ዩኒቨረሲቲው ምርምር የሚያደርግ ሲሆን በዚህ አውደ ጥናት የሚቀርቡት በዚህ የምርምር ማዕቀፍ ስር የተሰሩት ጥናቶች የችግሩን ጥልቀትና ስፋት የሚያስረዱ በመሆናቸው ተሳታፊዎች በውይይቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪአቸውን አቅርበዋል፡፡
በአውደ-ጥናቱ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር አለማየሁ ደበበ ለአውደጥናቱ ተሳታፊዎች ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጣቸው የትምህርት፣ የስልጠናና የማማከር እንዲሁም የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ የቆየ መሆኑን አስታውሰው ይህን ትብብርና በቅንጅት የመስራት ባህል የበለጠ ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የዚህ ጥረት አንዱ ማሳያ የሆነው ይህ ዓመታዊ የምርምር አስተችቶት አውደ ጥናት አንዱ ሲሆን በዚህ የምርምር አስተችቶት ላይም በሀገራችን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም በእያንዳንዳችን የግል ህይወትም ጭምር ሳይቀር ትልቅና አሉታዊ የሆነ ተጽዕኖ በማሳደር ላይ የሚገኙትን ሁለት አደጋዎች ማለትም ሙስና ወይም ንቅዘትን እና ድለላን የዚህ አውደ ጥናት ዐብይ ትኩረት በማድረግና በምርምር በመዳሰስ ለመንግስት የፖሊሲ ግብዐት የሚሆን ምክረ ሀሳብ ለማቅረብ በማሰብ የምርምር ስራዎቹ ቀርበዋል ብለዋል፡፡
ሙስናን በተመለከተ ዘጠኝ የምርምር ስራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አለማየሁ እነዚህ ጥናቶችም ትኩረታቸውን ያደረጉት በህዝብ ጤና አገልግሎት፣ በከፍተኛ ትምህርት፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በፈቃድና ሰነድ ሰጪ አካላት፣ በትራንስፖርት ዘርፍ፣ በመንግስት ግዥ እና ህብረተሰቡ ሙስናን ከመዋጋት አንጻር ያለው ቁርጠኝነትና የመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን ድለላን በተመለከተም የተካሄዱ አስር ጥናቶችም አሁን ያለው የድለላ ሥራ በግልና በማህበራዊ ህይወት ላይ “ምን አይነት ተጽዕኖ እያደረሰ ይገኛል?” የሚለው በጥልቀት የተዳደሱና ድለላ በከተማ ቤቶች ፣ ድለላ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ፣ በሰነድና ፈቃድ ሰጪ ተቋማት ውስጥ ያለ ድለላ፣ በብድር አቅርቦትና የፋይናንስ አገልግሎት ውስጥ ያለ ድለላን ወዘተ. ትኩረት ተሰጥቶባቸው የተጠኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም ሁለት ቀጥታ የውጪ ኢንቨስትመንት መሳብ ላይ የተሰሩ ጥናቶችም የአውደ ጥናቱ አካል ሲሆኑ በአጠቃላይ ጥናቶቹን ለማከናወንም ከ117 የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መረጃ የተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀረቡት ጥናቶችም ላይ የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በንቃት በመሳተፍ ግብረ መልስ እንዲሰጡበትና ጥናቶቹ የተሻሉ ሆነው ለመንግስት የፖሊስ ግብዐትነት እንዲውሉ ለማስቻል ሁሉም የጉባኤው ተሳታፊዎች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅረበዋል፡፡
ለአውደ ጥናቱ የተዘጋጁት ጥናቶችም በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የተሰሩ ሲሆኑ በተዘጋጀው ትይዩ መድረክ አማካይነት ለተሳታፊዎች ቀርበው በተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቶባችዋል፡፡