ኢሲሰዩ የሰራተኞች ድልድል እያካሄደ ይገኛል
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት በትምህርት በስልጠናና የማማከር አገልግሎት እንዲሁም በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችም በማከናወን የሀገሪቱን የሲቪል ሰርቪስ ሴክተር አቅም የመገንባት ተልእኮን በብቃት ሲወጣ የቆየ ሲሆን በዚህም ከሃምሳ ሺህ በላይ በሀገሪቱ የፌዴራልና የክልል ተቋማት እንዲሁም የከተማ መስተዳድሮች ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦን ያበረከቱ እና በማበርከት ላይ የሚገኙ ምሩቃንን አፍርቷል፡፡
ይህን ሀላፊነቱም ከጠቅላይ ሚኒስተትር ጽ/ቤትን ጨምሮ ለተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተጠሪ በመሆን ሲያከናውን የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በተደረገው አዲስ አደረጃጀት ዩኒቨርሲቲው ተጠሪነቱ ለኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር እንዲሆን የተደረገ ሲሆን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ባካሄደው አዲስ የዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ እና ምደባ ዩኒቨርሲቲው አሁን ባለው ቁመናና ደረጃ ተገምግሞ ከቀደምትና ከመጀመሪያው ትውልድ (First Generation) ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ምድብ ስር ተመድቧል፡፡
በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ለምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ባዘጋጀው አዲሱ መዋቅር መሰረትም በሶስት ዘርፎች ማለትም አስተዳደርና ልማት ዘርፍ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዘርፍ እና የምርምርና ትብብር ዘርፍ የተዋቀረ ሲሆን ተልዕኮውን በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስፈልገውን የመዋቅር ስራ አጥናቆ ከየካቲት 13 ቀን 2015ዓ.ም ጀምሮ ሰራተኞችን በመደልደል ላይ ይገኛል፡፡ በእስካሁኑ ክንውንም በአካዳሚክ ዘርፍ ውስጥ በሚገኙ የ69 የሀላፊነት መደቦች ብቃትን መሰረት ያደረገ (merit based ) ግልፅ ውድድር በማድረግ ሀላፊዎችን የመመደብ ስራ አጠናቋል፡፡
በአስተዳደርና የማኔጀመንት ድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ስር የሚገኙ የስራ ሀላፊዎችና የፈጻሚዎች ድልድልም ትልቅ ትኩረት በመስጠት ለሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ የግማሽ ቀን ገለፃ በማካሄድ ሰራተኛዉ ሙሉ በሙሉ በመመሪያ “859/2014 የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች መዋቅራዊ አደረጃጀት ለዉጥ መሰረት የመንግስት ሠራተኞች የድልድል አፈጻጸም መመሪያ” ላይ ግንዛቤ እንዲኖረዉ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችም እንዲብራሩተደርጓል፡፡
በግንዛቤ ማስጨበጫ ዉይይት ላይ የኢሲሰዩ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ እንደገለጹት የአቅም ገንቢ ተቋም በመሆናችን ወደፊትም በተለይ የሰራተኞቻችን አቅም ለመገንባት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የነጻ ትምህርት እድል አሁን ከሚሰጠዉ ቁጥር የበለጠ እንደሚሰጥ ዉጤቱም አሁን ላይ ሲታይ ከዚህ በፊት ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁ ሰራተኞቻችን ለድልድሉ ዝግጁ መሆናቸዉ እንደ አንድ እምርታ ይታያል ብለዋል፡፡
በተቀመጠዉ የግዜ ሰሌዳ መሰረት አጠቃላይ የሰራተኞች ድልድል ግንቦት 15/2015 ድረስ ይጠናቀቃል፡፡