ኢሲሰዩ የከተማ ማኔጅመንትና ትራንስፎርሜሽን ስልጠና ማዕከል ሰልጣኞችን አስመረቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ማኔጅመንትና ትራንስፎርሜሽን ስልጠና ማዕከል ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ከፌደራል የከተማ መሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ ለ177 ሰልጣኞችን በሐምሌ 01 ቀን 2014 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ አስመረቀ፡፡ ስልጠናው የመሬት በፍትሃዊነት ለአገር ልማት በሚል ለ45 ቀናት የተሰጠ ስልጠና ሲሆን ስልጠናውን የወሰዱ ሰልጣኞችም በተደረገላቸው ምዘና መሰረት ብቃታቸው ተረጋግጦ የዕውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቶአቸዋል፡፡
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይም የከተማና መሠረት ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ሰልጣኞችን ‹‹ለዚህ ቀን በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡›› በማለት ባስተተላለፉት መልዕክት ከተሞች የላቀ እድገት እንዲኖራቸው ዜጎች ሀብቱን በአግባቡ በመጠቀም አስፈላጊነት አመልክተው ይህን ለማሳካት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለያየ መልኩ ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን ክህሎት ተግባር ላይ በማዋል ፍሬአማ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የስልጠናና ማማከር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዋቅጋሪ ነጋሪ ለሰልጣኞቹ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ ‹‹ዛሬ የተገናኘነው ሰርተፍኬት ለመስጠት ብቻ ሳይሆን በስልጠናው መሰረት በቀጣይነት ምን መስራት አለብን የሚለውን ለመወያየት ጭምር ነው፡፡ ስራችንን ከማስዋባችን በፊት እራሳችንን ማስዋብ ይኖርብናል፡፡ ይህም ማለት ለራሳችንና ለሞያችን ያለንን ክብር በመረዳት ብልሹ አሰራር በማፅዳት ውብ የሆነ አገልግሎት ለማህበረሰቡ መስጠት ይጠበቅብናል ማለት ነው›› ብለዋል፡፡