ኢሲሰዩ የክረምት የወጣቶች ስልጠና ያጠናቀቁ ሰልጣኞችን አስመረቀ
---------------------------------------------------------
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በክረምት ልዩ የወጣት ሲቪል ሰርቫንቶች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መርሀ ግብር በመጀመሪያ ዙር ያሰለጠናቸውን ሶስት መቶ ወጣት ሲቪል ሰርቫንቶች የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ብርሀኑ ፈይሳ እና የዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነሐሴ 6 ቀን 2013 ዓ.ም በአባይ አዳራሽ አስመርቋል፡፡ ስልጠናው “ብቃት ያላቸው፣ በስነ ምግባር የታነፁ እና የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ የተላበሱ ወጣት ሲቪል ሰርቫንቶችና ሴቶችን በፐብሊክ ሴክተሩ ውስጥ ማፍራት” በሚለው የዩኒቨርስቲው ስትራቴጂክ ግብ መሰረት የተዘጋጀ ስልጠና ነው፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ ብርሀኑ ፈይሳ ለተመራቂዎች ባደረጉት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ሰልጣኞች ስለ ህይወት ክህሎት በትምህርትም ሆነ በተለያየ መልኩ ያካበቱት በርካታ ቁም ነገር መኖሩን ጠቁመው ይህ ስልጠናም ቀደም ሲል የነበራቸውን እውቀት አውጥተው ጥቅም ላይ እንደሚያውሉ ለማድረግ እንደሚረዳቸው ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል፡፡ ሰልጣኞችም የስራ ስነምግባርን በመጠበቅ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመለወጥ ስልጠናው እሴት የሚጨምር መሆኑንና ሰልጠኞችም በስራ ህይወታቸው በዚሁ መልክ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የስልጠናና ማማከር ዘርፍ ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ዋቅጋሪ ነጋሪ በበኩላቸው በስልጠናው ሂደት ላይ ሰልጠኞችም እንደ ሰልጣኝ፣ ዩኒቨርሲቲው እንደተቋም ብዙ ያተረፉ እርስ በርስ የተማማሩበት የትምህርት መድረክ የፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ “በዚህ የመጀመሪያ ዙር ስልጠና እኛ ያላየነውን ነገር እንድናይ ያደረጋችሁን ሲሆን እናንተም በህይወታችሁ ውስጥ ተጨማሪ ክህሎቶችን እንድታካብቱ አድርገናል፡፡ በዘጠኝ የስልጠና ርዕሶች ሀገራዊ ዳሰሳ በማድረግ ባዘጋጀናቸው የስልጠና ርዕሶች የተሰጡትን ስልጠናዎችም ተግባራዊ እንደምታደርጓቸው ሙሉ ተስፋ አለን፡፡” ብለዋል፡፡
ዶ/ር ልደቱ አምሳሉ ባደረጉት ንግግርም ተመራቂዎች በስራ ላይ በሚገጥሟቸው የተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት ከመከፋትና ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ደስታን ከውስጣቸው በማመንጨት በስራቸው ደስተኛ መሆን እንደሚገባቸው፤ የደስታ ምንጭም ከሰዎች የውስጥ ስሜት የሚመነጭ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ “በስራ ላይ በቀናነት እና በደስታ የምታገለግሉት ማህበረሰብ በስራችሁ በመርካትና ከእናንተ አገልግሎት በመማር በሄደበት ሁሉ ስለእናንተና ስለተቋማችሁ መልካምነት በማሰብ እርሱም መልካም ነገር መስራት ይጀምራል፡፡ እንዲህ ባለ መንገድ ሁላችንም ስራችንን በመውደድ ደስታን በራሳችን በማመንጨት ሀገራችንን ማገልገል ይገባል፡፡ የማንለውጠውን ነገር ለመለወጥ ከመታገል ይልቅ የምንለውጠው ላይ ብንሰራ ህይወት በራሷ ጣፋጭ ትሆናለች፡፡” በማለት መልዕክታቸውን ለተመራቂ ወጣት ሲቪል ሰርቫንቶቹ አስተላልፈዋል፡፡
የክረምት ልዩ የወጣት ሲቪል ሰርቫንቶች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መርሀ ግብር የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት በቀጣይ አስር ዓመታት በክረምት መርሀ ግብር አስር ሺ ወጣት ሲቪል ሰርቫንቶችን አቅም በቀጣይነት ለመገንባት የተዘጋጀ መርሀ ግብር ሲሆን ከእነዚህም መካከል በመጀመሪያ ዙር ያሰለጠናቸውን ሶስት መቶ ሰልጠኞችን በህይወት ክህሎትና እና ተዛማጅ የሆኑ ዘጠኝ የስልጠና ርዕሶች የተሰጠው ስልጠና በስኬት መጠናነቀቁ እና የሁለተኛ ዙር የስልጠና መርሀ ግብርም በተያዘው ፕሮግራም መሰረት የሚቀጥል መሆኑ ከፕሮግራሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡