ኢሲሰዩ የ2014 ክረምት የወጣቶች ስልጠና ያጠናቀቁ ሰልጣኞችን አስመረቀ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የ2014 ዓ.ም በልዩ የክረምት የወጣት ሲቪል ሰርቫንቶች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መርሀ ግብር በመጀመሪያ ዙር ያሰለጠናቸውን ሁለት መቶ አስራ ሁለት ሲቪል ሰርቫንቶችን ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም በአባይ አዳራሽ አስመርቋል፡፡ ሰልጣኞቹም በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ አስራ ሶስት የፌዴራል መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ ወጣት ሲቪል ሰርቫንቶች ሲሆኑ ለአሰራ አምስት ቀናት የተሰጠውን ስልጠናን በብቃት ማጠናቀቃቸው የተረጋገጠላቸው ሰልጣኞች ናቸው፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ የስልጠናውን ዓላማ አስመልክተው የክረምት የወጣቶች ስልጠና ፕሮግራም ሲቀረጽ ራዕይ የሰነቁ ፣ የሕይወት ዓላማ ያላቸው ፣ እንደግለሰብ ራሳቸውን ያነጹ፣ እንደ ማህበረሰብም ማህበራዊ ሚናቸውን የሚወጡ እንዲሁም እንደ ሀገር ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት የሚወጡ ወጣት ሲቪል ሰርቫንቶች ለማፍራት በማሰብ መሆኑን ጠቅሰው ሰልጣኞች ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጁትን ሞጁሎች በብቃት በማጠናቀቅ ለምረቃ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ለሰልጣኞቹ የመልካም ምኞት መልዕክታቸው አስተላልፈዋል፡፡ ፕሮፍሰር ፍቅሬ አያይዘውም ብቃት ያለው ሲቪል ሰርቫንት የሚባለው የመንግስት የልማት አቅጠጫ ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ በቂ ግንዛቤ ያለው፣ ሙያዊ ኃላፊነቱን በአግብቡ የሚወጣ፣ መብትና ግዴታውን በአግብቡ የሚወጣ ፣የግልና የቡድን ስራዎችን አጣጥሞ የሚያስኬድ፣ በዕቅድ የሚመራና ሙያዊ ሥነምግብር ያለው፣ ተነሳሽነትን የተላበሰና በቴክኖሎጂ የዳበረ ዕውቀት ያለው እና የመሳሰለሉትን ዐበይት መገለጫዎች የተላበሰ፤ ዝርዝር ጉዳዮች በአግባቡ የሚተገብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ሰልጣኞች በመደበኛው የዩኒቨርሲቲ የትምህርታቸው ያልዳሰሷቸው ነገር ግን በዕለት ተዕለት የስራ ህይወታቸው ላይ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችን የሚጨብጩበት እና ለቀጣይ የሥራ ሕይወታቸው መሠረታዊ የሆነ የብቃት ደረጃቸውን አንድ እርምጃ ከፍ የሚደርግና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚያግዛቸው ስልጠና የተሰጣቸው መሆኑን በማመልከት ሰልጣኞች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት በተግባር በመተርጎም ራሳቸውንና ተቋማቸውን ለመቀየር እንዲተጉ እንዲሁም በቀጣይነት የራሳቸውን አቅምም የማጎልበት ስራ መስራት እዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ለስልጠናው ሂደት መሳካት ተሳትፎ ላደረጉ የዩኒቨርሲቲው አባላትና ልዩ ልዩ ተቋማትም ላበረከቱት አስተዋጽኦ በዩኒቨርሲቲው ሥም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የስልጠናና ማመከር ዘርፍ ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ዋቅጋሪ ነጋሪ በበኩላቸው ሰልጣኞች በስልጠናው ያገኙት ዕውቀትና ከህሎት እንዳለ ሆኖ በቀጣይ ራስን የማብቃት ሥራ ላይ እንዲሁም ሀገርን እንዴት ወደተሻለ ደረጃ ከፍ የማድረግ አላማን በመያዝ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ አመልክተው ሰልጣኞች በየተቋሞቻቸው ያሉትን ጉድለቶችን በመለየትና እነዚያን ጉድለቶች በመለወጥ ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የክረምት የወጣት ሲቪል ሰርቫንቶች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ፕሮግራም አሰተባባሪ ዶ/ር አዜብ አሰፋ በበኩላቸው ሰልጣኞች በነበራቸው የአስራ አምስት ቀናት ቆይታ በተለያዩ ርዕሶች የተዘጋጁና በመሰረታዊ የብቃት ደረጃዎችን ለማምጣት የሚያስችሉ አምስት የስልጠና ሞጁሎችን ያጠናቀቁ መሆኑን ገልጸው በወሰዱት ስልጠናም የተወሰነ ለውጥ እንደሚያመጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ሰልጣኞችም ምንም እንኳን በርካታ የማይመቹና ውስብስብ ችግሮች ቢኖሩም በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ያላቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት በመገንዘብ ለአጠቃላይ የሲቪል ሰርቪሱ አገልግሎት ማደግ በተነሳሽነት መንፈስ መስራት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው በስልጠና የቀሰሙት እውቀትና ክህሎት በቀጣይ ሥራቸው የሰፋ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በስልጠናው የተሳተፉ አንዳንድ ሰልጣኞች የተሰጣቸውን ስልጠናና በዩኒቨርሲቲው የነበራቸውን ቆይታ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት የወሰዱት ስልጠናው ያላቸውን የህይወት ፍልስፍና እና ቀደም ሲል የነበራቸውን አመለካከት በእጅጉ የሚለውጥ መሆኑን እንዲሁም በቀጣይ ሥራም ሆነ የማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ስልጠና መሆኑን ገልጸው ስልጠናውን በማዘጋጀቱ ለዩኒቨርሲቲው ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡