ኢሲሰዩ የ2014 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ አደረገ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የ2014 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማውን የዘርፍ ም/ፕሬዚዳንቶች እና የዩኒቨርሲቲዉ የካዉንስል አባላት በተገኙበት ታህሳስ 28 ቀን 2014 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ አካሄደ፡፡
በግምገማዉ መክፈቻ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ለካውስሉ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ በዚህ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሁሉም የካዉንስል አባለት ክፍተቶችን በመለየት የነጠረ ሀሳብ እንዲያቀርቡ፤ በተለይ በ 6 ወር ዉስጥ የተከናወኑ እና ያልተከናወኑ ተግባራትን እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በዝርዝር በመለየት ለበለጠ የሥራ አፈጻጸም ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚቀመጡበት የግምገማ መድረክ መሆኑን በማሳሰብ ፕሮግራሙን አስጀምረዋል ፡፡
በማስከተል የየዘርፉ ም/ፕሬዚደንቶች (የአካዳሚክ ፣የስልጠናና ማማከር፣የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት እና የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ) የስድስት ወር አፈጻጸማቸዉን ለካውንስሉ አባላት በማቀረብ ከካዉንስል አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አባላቱም ሀሳባቸዉን ዘርዘር አድገዉ ያቀረቡ ሲሆን ለቀጣይ የሥራ አፈጻጸም አቅጣጫዎችንም አስቀምጠዋል፡፡
በግምገማው ማጠቃላያ ላይም ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ “ይህ ግምገማ እራሳችንን የምናይበት፣ ያልተተገብሩ እቅዶቻችንን ነቅሰን የምናወጣበትና ዕቅዶቻችንን ለማሳካት የበለጠ ሥራ የምንነሳሳበት ግምገማ ነው::” በማለት ለካውንስሉ አባላት የገለጹ ሲሆን በተለይ የኢሲሰዩ በቅርቡ በኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ሥር መካተቱን ተከትሎ ሌሎች ተጨማሪ ተልዕኮዎች ከመስጠት ይልቅ ዩንቨርስቲዉ ከዚህ በፊት የነበረዉን ተልእኮ ማለትም የሲቪል ሰርቪሱን አቅም መገንባት ላይ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል፡፡ በዚህም መሰረት የተሰጠን ተልዕኮ እንደሀገር ብቸኛ ተቋም የሚያደርገን በመሆኑ ከዚህ በፊት ከምንሰራዉ በተለየ መልኩ ሥራዎችን በብቃት መስራት ተገቢ መሆኑን የገለጹት ፕ/ር ፍቅሬ በመንግስት መዋቅሮች የሚሰሩ ሰራተኞች ላይ በተለይ የአቅም ግንባታና የአሰራር ማሻሻያ ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ፣ በስልጠናዉ፣ በትምህርት፣ በምርምምና በማማከር ተጨባጭ ለዉጥ ማምጣት ከተቋሙ እንደሚጠበቅ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አክለውም በትምህርታችን፣በስልጠናችን በምርምራችን ዙሪያ ወቅታዊ ትንታኔ ማድረግ እንደሚጠበቅ፣ በተለይ እንደሀገር ምን አይነት ሲቪል ሰርቫንት መኖር እንዳለበት ከብቃት ጋር በተያያዘ ትልቅ ስራ መሰራት እንደሚገባና ዘመናዊ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት ላይ የተቋሙ ሚና ጎልቶ መውጣት እንደሚገባው፣ በተለይ በሲቪል ሰርቪሱ ላይ የስብእና ግንባታ ላይ ትልቅ ስራ መሰራት እንደለበትና ሲቪል ሰርቪሱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እንዲሰጥ ድጋፍ ማድረግ ላይ ጠንክሮ መስራት ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል፡፡
በእነዚህ አበይት ጉዳዮች ላይ ትልቅ ስራ መሰራት እንዳለበት በአጽንኦት የገለጹት ፕ/ር ፍቅሬ ይህንንም ለማከናወን በተለይ በዩኒቨርሲቲዉ ሰራተኞች ላይ ትልቅ የአቅም ግንባታ ሥራ እንደሚሰራ እና እስካሁን እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ ተቋም ወይም ዩኒቨርሲቲ ሲባል ህንጻ ብቻ ሳይሆን ሰዉ መቅረጽ የሚችል አቅም ያለዉ የሰዉ ስብስብ መፍጠር መሆኑን መገንዘብ ተገቢ መሆኑን አበክረዉ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ዩንቨርስቲዉን ተወዳደሪ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎችን ዘርዘር አድረገዉ አብራርተዉ ለሚቀጥለዉ ሩብ ዓመት የሚሰሩ አንኳር ስራዎች ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ የእለቱን ግምገማ ተጠናቋል፡፡