ኢሲሰዩ የ2015 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ አደረገ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የ2015 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማውን የዩኒቨርሲቲዉ የካዉንስል አባላት በተገኙበት ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ አካሄደ፡፡
በግምገማዉ መክፈቻ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ለካውስሉ አባላት ባደረጉት ንግግር በየሩብ ዓመቱ ጊዜውን ጠብቆ ሲካሄድ የነበረው የካውንስል ስብሰባ እና የዩኒቨርሲቲው የስራ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በጥቅምት ወር በዩኒቨርሲቲው በተሰጠው የአስራ ሁለተኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ምክንያት ባለመካሄዱ በዚህ ስብሰባ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የሥራ ክንውንን ጨምሮ አጠቃላይ የስድስት ወር የአፈጻጸም ሪፖረትት ቀርቦ ግምገማ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ፕ/ር ፍቅሬ አክለውም ከታህሳስ 24 -27 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በዩኒቨርሲቲው የካውንስል አባላትና በአካዳሚክ ሠራተኞች “የምሁራን ሚና በሀገር ግናባታ” በሚል ርዕስ የምክክር መድረክ መካሄዱን አስታውሰው በተካሄደው የምክክር መድረክም ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ላይ የበለጠ ጠንክሮ መስራት ተገቢ መሆኑ የተመላከተበት መድረክ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ጉዳዮችም በሀገሪቱ የሚገኙ የተቋማት ግንባታ እና አዲስ የፖለቲካ ባህል ማምጣት መሆኑን የጠቀሱት ፕ/ር ፍቅሬ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሌሎች ተቋማትን አቅም የሚገነባ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የራሱንም አቅም መገንባት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በስራ ላይ ያለው የዩኒቨርሲቲ መዋቅር ተከልሶ እና የተከለሰውም መዋቅር ጸድቆ ወደ ተግባር የሚገባበት ደረጃ ላይ ይገኛል ብላዋል፡፡ በአዲሱ መዋቅር መሰረትም ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዩኒቨርሲቲነት የተመደበ በመሆኑ በሶስት ዘርፎች ማለትም አስተዳደርና ልማት ዘርፍ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዘርፍ እና የምርምርና ትብብር ዘርፍ የተዋቀረ መሆኑን የገለጹት ፕ/ር ፍቅሬ ዩኒቨርስቲውን ወደ ላቀ ከፍታ ለማሸጋገርና የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት እንዲችል ከምንጊዜውም በበለጠ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በማስከተል የየዘርፉ ም/ፕሬዚደንቶች (የአካዳሚክ ፣የስልጠናና ማማከር፣የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት እና የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ) እንዲሁም የፕሬዚደንት ጽ/ቤት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖረታቸውን ለካውንስሉ አባላት በማቀረብ የካውንስሉ አባላት በቀረበው ሪፖረት ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡