ኢሲሰዩ 2312 ተማሪዎችን አስመረቀ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (ኢሲሰዩ) በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን 2312 ተማሪዎች በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና በፒኤች ዲ በአደዋ ድል መታሰቢያ ፓን አፍሪካ የመሰብሰቢየ አዳራሽ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በድምቀት አስመረቀ፡፡ ከመደበኛ ፕሮግራሙ ባሻገርም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ባለው ትብብር በልዩ ፕሮግራም ሲያሰለጥናቸው የቆዩ 24 ዕጩ ዲፐሎማቶችንም በከፍተና ዲፕሎማ ሰርቲፊኬት አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ባስተላለፉት መልዕክት በሀገራችን የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች እየተተገበሩና ውጤት እያስገኙ መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን ሲንከባለሉ በቆዩና ከቅርብ ጊዜያት በኋላ በተነሱ አንዳንድ ክስተቶች ጋር ተያይዞ አጠቃላይ የሆነ የሞራል መናጋት ጋር ተያይዞ ፈርጀ ብዙ ችግሮች እየተፈታተነን እንገኛለን ብለዋል፡፡ በሪፎርምም እነዚህን ችግሮች በመፍታት፣ ብሎም አለም አቀፍ ችግሮችንም መቋቋም የሚችል መጪ ትውልድ ማዘጋጀት፣ በብቃትና በአንድነት መስራት የሚገባን ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ ትምህርት እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ ላይ የማይተካ ሚና የሚጫወት ቢሆንም የትምህርት ዘርፉ በትምህርት ጥራት እና ተያያዥ ጉዳዮች ያጋጠሙት ስባራቶችን የትምህርት ሪፎርም ተቀርጾ በመተግበር ላይ መሆናቸውን እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎች አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ነጻነትም ለማስገኘትም የራስገዝ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የራስገዝ አዋጅ ጸድቆ ተግባራዊ እየሆነ መሆኑን እና በትምህርት ሚኒስቴርም ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም በሀገራችን ያለውን የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ከተቋቋሙት ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን አስታውሰው ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ሲቪል ሰርቫንቶችን ማፍራቱን የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ ዩኒቨርሲቲው የተጣለበትን የፐብሊክ ሰክተሩን አቅም የመገንባትና የማዘመን ተልዕኮ ለመወጣት እንዲያስችለው ዩኒቨርሲቲውን በአዲስ መልክ ሪፎርም በማድረግ ሀገራዊ የልዕቀት ማዕከል ለማድረግና በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሲቪል ሰርቪስ የሰው ኃይል መገንባት የሚችል ተቋም እንዲሆን በመንግስት መወሰኑን ገልጸው ከትምህርት ሚኒስቴር ፣ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ባለሙያዎች የተዉጣጣ የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ዩኒቨርሲቲው እንደገና በአዲስ መልክ የማጠናከር ጥናት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ለሀገርና ለህዝብ ታማኝ የሆኑ ባለሙያዎች በልዩ ሁኔታ የሚፈሩበት ተቋም ይሆናል ተብሎ እንሚታመንም ገልጸው፤ በሚደረገው ሪፎርም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ፣ሰራተኞችና ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎችም ወደየተቋማቸው ሲመለሱ ከአድልዎና ከወገንተኝነት የጸዳ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡
የኢሲሰዩ ፕሬዚደንት ዶ/ር ንጉሥ ታደሰ በበኩላቸው ባደረጉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ለተመራቂዎቹ በብዙ ድካምና ጥረት ያገኛችሁት ውጤት በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ ዶ/ር ንጉሥ በማስከተልም የሀገራችን የፐበሊክ ሰርቪስ መንግስትና ዜጎች በሚጠብቁት ልክ ነጻና ገለልተኛ ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣን አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲም ከምንግዜውም በበለጠ ከኢፌዴሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በቅርበትና በቅንጅት የፐብሊክ ሰርቪሱን አቅም የመገንባት ጉዞውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከ34 ሺህ በላይ ምሩቃንን በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያዲግሪ፣በማስተርስና በፒኤች ዲ ዲግሪ ማፍራት የቻለ እና 448ምሩቃንን ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራ የመጡ የየፐብሊክ ሴክተር ተቋማት ሲቪል ሰርቫንቶችን በማስመረቅ ሀገራችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን መልካም ጉርብትናና የውጭ ጉዳይ መርህ በትምህርት መስክ እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማድረግ መቻሉን የጠቆሙት ዶ/ር ንጉሥ ከ200 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሲቪል ሰርቫንቶችና አመራሮችም ብቃት ተኮር ስልጠና በመስጠት ብቃታቸውን ለማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡በጥናትና ምርምር መስክም ከ500 በላይ ሳይንሳዊ የምርምር ፕሮጀክቶችን በማካሄድ በምርምር የተደረሰባቸውን ግኝቶችና አሰራሮች ለሚመለከታቸው የህዝብ አገልግሎት ተቋማት በማሰራጨት ለፖሊሲ ግብአት እንዲሆኑ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከመንግስት በተሰጠው ተልዕኮ መሰረት ከታዳጊ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የፐብሊክ ሴክተር ተቋማት እንዲጠናከሩ በልዩ ሁኔታ ፕሮግርም ቀርጾ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞች ያካሄደ እና ውጤት የስመዘገበ መሆኑንና ከተለያዩ ተቋማትም ጋርም በትምህርትና በስልጠና ፣የምርምርና ማማከርስራዎችተከታታይና ቀጣይነት ያለው አቅም በመገንባት ረገድ ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ንጉስ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲውየተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንዲችል ተቋማዊ፣ አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ነጻነት አስፈላጊ በመሆኑ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ የመሆን ዕቅድን መሰረት በማድረግ የሽግግር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና በዩኒቨርሲቲው የውስጥ ገቢውን ለማሳደግ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ለመፍጠር፣ ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማደራጀትና ስትራቴጂያዊ የሰው ኃይል አመራርን ለማጠናከር፣ተመራጭና ተወዳደሪ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞችን ለማልማት፣ አስቻይ የምርምርና ማማከር ስርዓት ለመዘርጋት፣ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ልማታዊ ፕሮጀክቶች ላይ ያለውን አበርክቶ ለማጠናከር፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰረተ ልማትና ፋሲሊቲዎች ለማደራጀት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማርና የአገልግሎት አሰጣጥ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ስርዓት ለማጠናከር በርካታ ቁልፍ ተግባራትን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑና በ2018 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀ የትምህርትና የስልጠና የልህቀት ማዕከል ለመሆን አልሞ ቁልፍ ተግባራትን በመለየት እየሰራ መሆኑን ገልጸው ፤ አለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞች መቅረጽና ተግባራዊ ማድረግ፣ የመማሪያና የስልጠና ክፍሎችን ማዘመን፣ የተጀመሩ ፋሲሊቲዎችን ማጠናቀቅና ወደተግባር እንዲገቡ ማድረግ፣ከሀገር ውስጥና አለማቀፍ መሰል ተቋማት ጋር ያለን ነባርትስስሮችን ማጠናከርና አዳዲስ ትስስሮችን የመፍጠር ስራዎች እንዲሁም ሌሎች ስራዎችም የሚከናወኑ መሆናቸውን እና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና ከሌሎች አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት በአዲስ መልክ የመቃኘትና ትብብሮችን የማጠናከር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚደረግ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡