ከከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ የአካዳሚክ ሠራተኞችና አመራሮች ጋር ሀገራዊና ተቋማዊ የትምህርት ሪፎርም ላይ ውይይት ተካሄደ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ አመራሮችና የአካዳሚክ ሠራተኞች በተቋማዊ የትምህርት ሪፎርም ስራዎች ላይ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም በህዳሴ አዳረሽ ውይይት አካሄዱ፡፡
በዉይይቱ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው በቅድሚያ ላላፉት 6 ዓመታት ኮሌጁ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ጥረት ላደረጉ የአመራር አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው አዲስ ለተመደቡ አመራሮችም ኮሌጁን ለማገልገል ፍቃደኛ ሆነው እና የነበረውን ዉድድር አሸንፈው ሪፎርሙን ለመተግበር ላሳዩት ቁርጠኝነት በማኔጅመንቱ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ፕ/ር ፍቅሬ ስለውይይት መድረኩ ዓላማ ሲገልጹም “በተለይ ዛሬ የተገናኘነው በትምህርት ሚኒስቴር እንደ ሀገር በትምህርት ጥራትና ተያያዥ ስራዎች ላይ አበራታች ለውጦችን ለማምጣት የሪፎርም እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ሲሆን የኛም ዩኒቨርሲቲ የሪፎርም ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ ለመስራት በተያያዥም በሀገር አቀፍና በዩኒቨርቲያችን የተደረጉ የሪፎርም ስራዎች ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፡፡ በተለየ የትኩረት መስክ ምርምር፣ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሰቲ መሆን፣ የትምህርት ጥራትና ተግባራዊነት ፣የምርምር ምርታማነትና ተፅኖ፣የማህበረሰብና አገልግሎት ተሳትፎ ፣ገቢ ማመንጨት፣የግምገማ ስርዓት፣ውህድ አመራር እና የሀብት ማፈላለግ ዙርያ ግንዛቤው እንዲኖራችሁ እና የትምህርት ሪፎርም ዙርያ በባለቤትነት ስሜት እንድትከዉኑ ለማድረግ በማሰብ የተዘጋጃ የዉይይት መድረክ ነዉ፡፡” ብለዋል ፡፡
በማስከተል ፕሬዚዳንቱ ሲገልጹ ላለፉት 28 ዓመታት ተቋማችን በሲቪል ሰርቪስ አቅም ግንባታ ላይ በትምህርት፣ በስልጠና ፣በምርምር እና በማማከር ዘርፎች ላይ በትኩረት ሲሰራ እንደቆየና አሁን ለደረሰበት ምዕራፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን በመግለጽ የተቋሙ ተጠሪነት ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ከተዘዋወረ ጊዜ ጀምሮ በተለይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የትኩረት መስክ ልየታ በተቀመጠዉ መስፈር (ከሚሰጧቸው ፕሮግራም 80% የ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም መሆን፣የስታፍ ፕሮፋይል ከ50 % በላይ ሶስተኛ ድግሪ ያለው መምህር አንዲሆን እና በሌሎችም መስፈርች) መሰረት የኢሲሰዩ በአጠቃላይ ካሉት 9 የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን ችሏል፡፡ እኛም እንደተቋም ይህ ትልቅ ስኬት ስለሆነ ደስታ ይሰማናል ፡፡ ስለዚህ አሁን የዩኒቨርሲቲያችን የትኩረት መስክ አንዱ ምርምር እንደመሆኑ መጠን ትልቅ የቤት ስራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡ ስለዚህም ይህ ኮሌጅ “ወዴት እየሄደ ነው? የምርምር ዩኒቨርሲቲ መስፈርትን ሙሉ ለሙሉ ለማሟላት ምን ይጠበቃል?” በሚሉ ጉዳዮች ዙርያ ሁላችንም የጋራ አድርገን ወደስራ የምንገባበት ወቅት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ብለዋል፡፡
ፕ/ር ፍቅሬ አክለውም በ2016 የትምህርት ዘመን እንደኮሌጅ ሊከናወኑ የሚገባቸው አብይት ተግባራትን አስመልክተው፡-
1ኛ. የምርምር ውጤታማነት በዋናነት የሚለካው በተማሪዎች እና በመምህራን የሚሠሩ ምርምሮች እንደመሆኑ መጠን በእነዚህ የምርምር ስራዎች ላይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በጥራት ማከናወን፤
2. የመንግስት ዩኒቨርሰቲዎች እንደ ሀገር ራስ-ገዝ እንዲሆኑ አቅጣጫ የተቀመጠ በመሆኑ እንደ ኮሌጅ ማህበረሰብ በዋናነት በሁለንተናዊ፣ አንፃራዊ፣ አስተዳደራዊ ነፃነት እንዲኖረው የማድረግ ተልዕኮን በሚወጣበት ወቅት በመመሪያ፣ በደንብ፣ በነፃነት የትምህርት ስራ፣ የምርምር ስራ ሌሎች አስተዳደራዊ ነፃነቶችን እንዲጎናጸፍ፤ ዩኒቨርሲቲውን ተመራጭና ተወዳዳሪ ዩኒቨርሲቲ የማድረግ ስርዓት መዘርጋት፤
3. በሰራተኛው ዘንድም እራስን በማየት የምርምር ዩኒቨርሰቲ ስታፍ ለመሆን የሚጠበቁ ክህሎቶች ሙሉ ለሙሉ ማዳበር ፤
4. በመንግስት እንደ ሪፎርም የተያዘውን በትምህርት ጥራት ላይ ጠንከር ያለ አቋም በመያዝ ከተማሪ ቅበላ አንስቶ ትላልቅ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን የቅበላ ፖሊሲያችንም በሚገባ ተስተካክሏል፡፡ በዚህ መሰረት ብቁ ተማሪዎችን የማፍራቱን ኃላፊነታችንን በትጋት መወጣት፤
ኮሌጁ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ ዐበይት ጉዳዮች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ለማረጋገጥ ብዙ ስራዎችን የምንሰራ ይሆናል ብለዋል፡፡
የስርዓተ ትምህርት ክለሳ፣ አዳዲስ ስርዓተ ትምህርት ቀረፃ ፣ ተማሪ ቅበላ የማስተማሪያ ዘዴ፣ የምዘና አተገባበር፣ በምርምር ስራ ላይ መሳተፍ ጭምር ለትምህርት ጥራቱ ግብዓት ስለሚሆን በእነዚህ ነጥቦች ላይ ጠንከር ያለ ስራ ሰርተን ብቁ ምሩቅ እናወጣለን፡፡ ይህ ደግሞ በዋናነት የመምህራንን ብቃት፣ ተነሳሽነት እና ኃላፊነትን መወጣት እንዲሁም ልዩ ድጋፍ ከማድረግ ጋር የሚቀናጅ በመሆኑ በዚህ ረገድ ሁላችንም የየራሳችንን ሀላፊነት በአግባቡ መወጣት አለብን የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡
ስለ ትምህርት ጥራት ስናነሳ ሰፊና ትልቅ ስራ ይጠብቀናል ያሉት ፕሮፌሰር ፍቅሬ የምርምር ዩኒቨርሰቲ ሆነን ለመቀጠል ስራዎቻችን መመስከር ስለሚገባቸው እራሳችንን በበቂ ሁኔታ በማዘጋጀት እና ለዚህም ስራ በየትምህርት ክፍሉ ያሉ መምህራን የምርምር ስራ የግድ (Mandatory) መሆኑን በመገንዘብ በተደራጀ መልኩም ስራዎችን መስራት አስፈላጊ በመሆኑ የምርምር ስራዎች በግልና በቡድን መስራት ተገቢነትን አስምረዉበታል፡፡
ሙያዊ ተሳትፎ ማድረግ ለማህበረሰብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው በመጠቆምም የምርምር ባህል ሊዳብር የሚችለው በዋናነት የልምድ ልውውጥ በማድረግ፣ ሴሚናርና ወርክሾፖች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎትን ሙያዊ አገልግሎት በማድረግና በዚህም ሂደት ዩኒቨርሲቲያችንን አሳድገን እኛም እንደግለሰብ ተጠቃሚ መሆን ይገባናል ብለዋል፡፡
ግምገማ በተመለከተም በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት 60 % ማስተማር 25 % መመራመር እና 15 % ደግሞ ማህበረሰብ አገልግሎት ዋናው የመገምገሚያው መስፈርት እንሚሆን ገልጸው ለ2016 ትምህርት ስራ ቅድመ ዝግጅት ቀጣይ አቅጣጫ የሚቀመጥ መሆኑን እንዲሁም ጠናካራ አመራር ፣በጋራ የሚሰራና የሚያቀናጅ ሁሉም ስራዎች ባለቤት ያላቸው ስራዎች እንዲሆኑ መደረጉንና በተቋሙ ለሚሰራው ኢንሼቲቭ ራስን የማዘጋጀት አስፈላጊነትን ከወዲሁ አሳስበዋል፡፡ ለዚህም አቅሙም እንዳለ በስራዎቻችን አይተናል ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ በማስከተልም “አስገዳጅ ስርዓት ዘርግተናል፡፡ እራሳችሁም እደጉ ዩኒቨርሲቲውን አሳድጉ ለዚህ ደግሞ ዩኒቨርሲቲው የሚፈልገውን ግብዓት ያሟላል፤ ምቹ ሁኔታም ይፈጠራል፡፡ በዚህም ከምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ግምባር ቀደም ለመሆን ስራችንን መስራት አለብን፡፡ አዲስ አመራር አዳዲስ ኢንሼቲቭ ይዞ ሠራተኛውን በማነቃቃት ስራዎችን መስራት ይገባዋል፡፡” ብለዋል፡፡ ከፍተኛ አመራሩም ለዚህ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል እንደሚገቡ አሳውቀዋል፡፡
በመጨረሻም ከታዳምያኑ ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶት ፕሬዚዳንቱ ምላሽና ማብራሪያዎችን ሠጥተውባቸዋል፡፡