የሀገር መንግስት ግንባታ የምሁራን ሚና የውይይት መድረክ በኢሲሰዩ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ‹‹በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና›› በሚል ርዕስ እየተካሄደ ያለው ሀገር አቀፍ ውይይት ታህሳስ 24 ቀን 2015 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ ተጀመረ፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተመስገን ቡርቃ ስለውይይቱ አስፈላጊነት ሲያብራሩ አሁን ባለው የዓለማችን ነባራዊ ሁኔታ ከምንግዜውም በላቀ ሁኔታ ሀገራት በጥንቃቄ የሚመሩበት መሆኑን አመልክተው ሀገራችን ኢትዮጵያም ካለችበት የጂኦፖለቲካል ሁኔታ ካላት የዳበረ ታሪክና የሰው ሀብት እንዲሁም በዓለማችን ላይ ያሉ ትላልቅ ሀገራት በዙሪያችን የጦር ሰፈር የመገንባት እንቅስቃሴና የራሷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በምታደርገው ጥረት እየደረሰባት ባለው ተፅዕኖ ምክንያት ምሁራን ሊወጡት የሚገባው ሚና እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በዚህም ረጅም የሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪክ ያለው ሀገር በአንዳንድ ክስተቶች ሀገር ችግር ውስጥ የሚገባበት ምክንያት ምንድን እንደሆነ፣ በትምህርት ስርዓታችን ውስጥም ምን እንደጎደለ እንዲሁም ውስጣዊ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ምሁራን የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ የሚያደረግ ውይይት መሆኑን በማስገንዘብ ተሳታፊዎች በውይይቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አሳስበዋል፡፡
ፕ/ሮ ፍቅሬ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ለውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የውይይት መድረኩ ምሁራን ለሀገር ስልጣኔና ዕድገት ጉልህ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን በማብራራት የሀገራችን መፃኢ ዕድል በእጃችን ላይ እንዳለ በመገንዘብ ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታችንን መወጣት ይገባናል ብለዋል፡፡
በመቀጠልም በዶ/ር ለማ ጉዲሳ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ‹‹በሀገረ መንግስት ግንባታ የምሁራን ሚና›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሀገራዊ ሰነድ ቀርቦ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እየተወያየበት ይገኛል፡፡
ውይይቱ በሁለት ክፍሎች የሚደረግ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል ታህሳስ 24-25 ቀን 2015 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ካውንስል ከተደረገ በኃላ ታህሳስ 26-27 ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ሰራተኞች የሚደረግ ይሆናል፡፡