የስልጠናና ማማከር ዘርፍ በሴክተር-ተኮርና የብቃት-ተኮር የስልጠናና የማማከር አገልግሎት አሰጣጥ ዙርያ አውደ-ጥናት አካሄደ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የስልጠናና ማማከር ዘርፍ ‹‹በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሴክተር-ተኮርና የብቃት-ተኮር የስልጠናና የማማከር አገልግሎት አሰጣጥ ፤ ፋይዳና የወደፊት አቅጣጫ›› በሚል ርዕስ በቀን ታህሳስ 4 ቀን 2015 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ አውደ-ጥናት አካሄደ፡፡
የአውደ ጥናቱ ዋነኛ ትኩረትም የመንግስት ሰራተኞችን አቅም በመገንባት ረገድ በተቋሙ እስከአሁን ምን ምን ተግባራት እንደተከናወኑ ግንዛቤን በመያዝ በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት ግልጽ የሆነ አቅጣጫ በማስቀመጥ ለመንቀሳቀስ ያለመ ሲሆን በአውደ ጥናቱ ላይም የተለያ የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ የስልጠናና ማማከር ዘርፍ ም/ል ፕሬዚደንት ዶ/ር ዋቅጋሪ ነጋሪ የአውደ ጥናቱ ተሳተፊዎቸን በአውደ ጥናቱ ላይ በመገኘታቸው አመስግነው በጋራ በመመካከርና ለወደፊት ስራዎችን በጋራ አቅዶ ለማሳካት አውደ ጥናቱ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ዋቅጋሪ አክለውም ‹‹ሴክተርና ብቃት ተኮር ስልጠናና ማማከር አገልግሎት መስጠትን ስናስብ ከተለመደው አስተሳሰብ በመውጣት አዲስና የአሰራር ስርዓትን የሚለውጥ አስተሳሰብ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡›› ብለዋል፡፡
በመቀጠልም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሴክተር-ተኮርና የብቃት-ተኮር የስልጠናና የማማከር አገልግሎት አሰጣጥ ፤ ፋይዳና የወደፊት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የውይይት መነሻ ጽሁፍ በወ/ሮ ሰብለ ሙሉጌታ የባለ ብዙ ዘርፍ ስልጠናና ማማከር ማዕከል ዳይሬክተር የቀረበ ሲሆን ዘርፍ በስሩ በሚገኙት አራት የስልጠናና ማማከር ማዕከላት አማካይነት በርካታ ተግባራትን ማከናኑንና ያስመዘገበውን ውጤት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም ወ/ሮ ኤደን ቡሽራ የስልጠና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው ዘርፉ በስልጠናና የማማከር አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከዚህ ቀደም ይከተለው የነበረውን አካሄድ በመገምገምና ክለሳ በማድርግ የብቃት ተኮር የስልጠና አሰጣጥ ሥነ-ዘዴን ለመተግበር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በቀረበው መነሻ ጽሁፍ ላይ ከአውደ ጥናቱ ተሳታፎች የተለያዩ ሀሳቦችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በተነሱት ሀሳቦች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡