የኢሲሰዩ ለሰራተኞቹ ያስገነባዉን ዘመናዊ አፓርትማ የቁልፍ ርክክብ አካሄደ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለሠራተኞች ያስገነባዉን ሁለት G+ 10 አፓርትማ በ 16/10/2015 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲዉ አባይ አዳራሽ የቁልፍ ርክክብ አካሄደ፡፡
በርክክቡ ወቅት የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ለሰራተኞቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክ በማስተላለፍ ይህ ፕሮጀክት ወደ 300 ሚ ብር የሚጠጋ ወጪ የተደረገበት ሲሆን ሁለት G+ 10 አፓርትማ ያሉት በአጠቃላይ 175 አባወራዎችእና እማወራዎች የሚኖሩበት ለትዉልድ የሚሻገር አሻራ ነዉ ብለዋል፡፡
ለአንድ ተቋም እድገት የሠራተኛዉ ሚና የማይተካ ሲሆን ለዚህም እንደተቋም የተሻለ እና ምቹ አካባቢ መፍጠር ግድ ይላል ስለዚህ ይህ ፕሮጀክት ሲጀመር በዋናነት አላማ አድርገን የተነሳዉ ሰራተኞች ባሉበት በተረጋጋ መንፍስ የተሻለ እና ዉጤታማ ሥራ እንዲሰሩ፤ በተጨማሪም ያለባቸዉን የቤት ችግር ለመቅረፍ ታቅዶ የተጀመረ ፕሮጀክት ነዉ ብለዋል፡፡ አያይዘዉም ሲገልጹ ፕሮጀክቱ ብዙ ዉጣ ዉረዶች ያለፈ ሲሆን ዛሬ የልፋታችን ዉጤት በዚህ መልኩ ስናየዉ ደስታችን የላቀ ፤ድካማችንን ያስረሳ ስኬት ነዉ ሲሉ ገልጸዋል ፡፡በተለይ ሀገሪቷ ካሏት ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ በምርምር ዩኒቨርሲቲነት መመደባችን እንደተቋም ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ የምንገኝ ሲሆን ለዚህም የተጠሰጠን ሀላፊነት በተመቻቸ ሁኔታ ሆነን ለማስፈጸም ይህ ፕሮጀክት ትልቅ አበርክቶ አለዉ ሲሉ ገልጸዋል ፡፡አላማችንን ለማሳከት ጉልበትና አይምሮአችንን ሳንቆጥብ በተፈጠረልን ምቹ ሁኔታ በተቋማችን ብሎም በሀገራችን የሚታይ ለዉጥ ማምጣት ግድ ይላል ስለዚህ ከዚህ በፊት ከምንሰራዉ ሥራ እጥፍ ተቋሙ ከሰራተኛዉ እንደሚጠብቅ መገንዘብ አለብን ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ሠራተኞች የተቋሙ ማናጅመንት ከፍተኛ ሀላፊነት በመዉሰድ ይህን ፕሮጀክት እዉን በማድረግ ለዚህች ዉጤታማ ቀን በማድረሳቸዉ ምስጋና አቅርበዋል ፡፡ እንዲህ አይነት ምቹ ሁኔታ የተቋሙ ሀላፊዎች በመፍጠራቸዉ ሠራተኛዉን በስራዉ አካባቢ ተረጋግቶ መስራት የሚያስችል፣ ያለበትንም ጫና የሚቀንስ እና የተሰጠዉን ሀላፊነት በተሳካ ሁኔታ ለመፈጸም የሚያስችል ልዩ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡