የኢሲሰዩ ሴኔት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ አካሄደ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን በ18/07/2015 ዓ.ም በሴኔት አዳራሽ አዲስ በተመረጡ የሴኔት አባላት በተገኙበት አካሄደ፡፡
የኢሲሰዩ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ በዚህ ስብሰባ መክፈቻ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸውን በማድረግ በተለይ አዲስ ለተመረጡ የሴኔት አባላት መልካም የስራ ጊዜ ተመኝተዋል፡፡በንግግራቸው ላይ አበክረዉ እንድተናገሩት ይህ ስብሰባ ለተቋማችን ታሪካዊ ስብሰባ መሆኑን ይህንንም ያልንበት ዋነኛ ምክንያት 1ኛ፡- የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 28 ዓመታት ሲሰራቸው የነበሩ የትምህርት፣የምርምር እና ስልጠና ስራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ በመሆኑ ተቋማችን በትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲዎች አመዳደብ በሀገራችን ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ ምደባ ሲደረግ ከጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች ጎራ የድህረ ምረቃና ምርምር ዩኒቨርሲቲ ምደባ ውስጥ መመደባችን፤ በ2ኛ፡- ዩኒቨርሲቲው የመንግስት ተቋማት የሠው ሀይል አሰራርና አደረጃጀት በሚያፀድቀው የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሰው ኃይል አደረጃጀታችን በሙሉ ፀድቆ ወደ ተግባር የገባንበት ወቅት ሲሆን 3ኛ፡- በአዲስ መልክ ለተዋቀረዉ አደረጃጀታችን አዳዲስ አመራሮች ከልዩ ተልዕኮ ጋር ብቃት ተኮር ውድድር በማድረግ ምደባ ያደረግንበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡ ይህ እንደ ተቋም ትልቅ ስኬትና ጥንካሬያችን የሚያሳይ ሂደት ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በማስከተልም ፕሬዚዳንቱ በአዲሱ መዋቅር ሴኔቱን የተቀላቀሉ አባላት በተለይ በአመራር እርከን ስለሴኔቱ አደረጃጀት ሲያብራሩ የኢሲሰዩ ሴኔት የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ መሰረት አድርጎ የተዋቀረ ሲሆን በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲዉ (legislation) የሚመራ መሆኑን በማስረዳት የሴኔት የስራ ድርሻ ምን ምን እንደሆነ በዝርዝር ገለፃ አድርገዋል፡፡ በዚህም ገለፃቸው የሴኔት አባላት አደረጃጀት፣ የሴኔት አባላት ቋሚ ኮሚቴ ተግባርና ኃላፊነት በዝርዝር ገለጻ አድርገዋል፡፡በማስከተልም በተለያዩ ምክንያት በጎደሉና የስራጊዚያቸዉን ባጠናቀቁ የሴኔት ስራ አስፈፃሚ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የማሟያ ምርጫ ተካሂዷል፡፡
2015 ዓ.ም አንኳር የተቋሙን ክንዉኖች ሲያብራሩ “ተቋማችን በዘንድሮ የትምህርት ዓመት ከሰራቸው ትልቅ እመርታ የተማሪዎቻችን የምርምር ስራ ውጤታማ እና ከምርምር ስራ ስርቆት ‘plagiarism’ የፀዳ ለማድረግ የ plagiarism software በመግዛት ሁሉም ተመራቂዎቻችንን የምርምር ውጤት የራሳችው የስራ ውጤት መሆኑን የሚገመገምበትና የምናረጋግጥበት አሰራር ዘርግተናል ፡፡የተመራቂ ተማሪዎቻችን የምርምር ስራዎች በአስገዳጅ ሁኔታ በዚህ ሶፍተዌር ማለፍ እንዳለበት፤ ይህ አካሄድ እውነተኛ ያልተኮረጀ የምርምር ስራ ተማሪዎቻችን እንዲሰሩ እና አማካሪዎቻችንም ጥራት ያለው ማማከር እንዲተገብሩ እገዛ የሚያደርግ በመሆኑ ትልቅ አበርክቶ አለዉ፡፡ በተጨማሪም ተመራቂ ተማሪዎች ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ሀላፊነታችሁን እንድትወጡ አሳስባለሁ::’’ ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ለላቀ ለውጥ ትልቅ ስራ መስራት ተጨማሪ ግዜ መስዋእት ማድረግ ያስፈልጋል ፤ ተቋም ሲያድግ ግለሰብ ያድጋል በተጨማሪም አቅም ያዳብራል ስለዚህ የጋራ ትብብር ለቀጣይ ለምናከናዉናቸዉ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እና ውጤታማ ተልዕኮዎች ለማስፈፀም ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ እቅዶች ቆጥረን እንደምንሰጠው ቆጥረን ውጤት እንደምንቀበል ከወዲሁ ሁሉም ሊገነዘበውና ሊፈጽም ይገባል ብለዋል፡፡
ዶ/ር አብረሀም ሐጎስ የእቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የአካዳሚክ አመራሮች አዲስ ስምሪት በተመለከተ ለሴኔት አባላት ሲያብራሩ ዩኒቨርሲቲዉ የትምህርት ሚኒስቴርን የአካዳሚክ ሰራተኞች የስራ ስምሪት አሰጣት /60-25-15/ 60% የስልጠና ፣ 25% የምርምር እና 15% የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ መሰረት በማድረግ በተጨማሪም የተሟላ የሰው ኃይል ፕሮፋይል በማደራጀትና ዲጂታል ዳታ ቤዝ በመፍጠር እና ስራዎችንም በጥብቅ ዲስፕሊን መፈፀም ግዴታ በመሆኑ ለዚህ የሚያስፈልጉ ዝርዝር ቅንጅታዊ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በአግባቡ የአካዳሚክ ሰራተኞቻችን ስምሪት በተለይ የመማር ማስተማር፣ ምርምርና ስልጠና ስራዎቻችንን መሰረት በማድረግ በአዲስ የተደራጀ ሲሆን የትምህርት አግባብነትና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ድልድል እንደተደረገ ገልፀዋል፡፡
ተቋማችን በአዲሱ አደረጃጀት በ3 ኮሌጅ ማለትም አመራርና አስተዳደር ኮሌጅ ፣የፋይናንስ ልማትና ማኔጅመንት ኮሌጅ፣ የከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ እና በሕግ ትምህርት ቤት እና የስልጠና ኢንስቲትዩት የተደራጀ ሲሆን በአጠቃላይ 330 የአካዳሚክ ሰራተኞች ሲኖሩን ከእነዚህ ዉስጥ ከ161 በላይ 3ኛ ዲግሪ ያላቸው መምህራን እንዳሉ በአጠቃላይ በተቋሙ 53 የትምህርት ፕሮግራሞች እንደሚሰጡ በዝርዝር ለሴኔት አባላቱ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ዳይሬክተሩ የአመራሩን ሀላፊነት ሲያብራሩ የሰው ኃይል በአግባቡ አሰባስቦ ስምሪት መስጠት፣ ክትትል ማድረግ እና በአግባቡ ማስፈጸም የአመራሩ ድርሻ ሲሆን ለስራዎቻችንም ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ ስላለዉ በአዲሱ አደረጃጀታችን የምርምር ውጤታማነት፣ የትምህርት ውጤታማነት እና የስልጠና ውጤታማነት ለማስቀጠል ባለቤትነትን ከኃላፊነት ጭምር ተቋሙ በአሰራሩ የዘረጋ ሲሆን በትምህርት ክፍሎች የአደረጃጀት ለውጥ ምክንያት በተደራጀ እና የአካዳሚክ ሰራተኞች የትምህርት ደረጃ ባገናዘበ መልኩ የሰው ኃይል ስምሪት በየትምህርት ክፍሉ እንደተደረገ ከዚህም ጋር በተገናኛ አጠቃላይ የስራ ስምሪት እንደተደረገ አስተዋዉቀዋል፡፡
በመጨረሻም ለምርምር ስራ ወጥነት የሚያገለግ( Graduate Research Policy and Guideline እና Graduate Thesis and Desertation Writing Guideline) የሚሉ መመሪያዎች ፀድቋል፡፡