የኢሲሰዩ ካውንስል የግማሽ ዓመት የእቅደ አፈጻጸም ግምገማ አደረገ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የመደበኛና የሪፎርም ሥራዎች አፈጻጸም የግምግማ መድረክ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ አካሄደ፡፡ በግምገማ መድረኩ ላይም የአካዳሚክ ጉዳዮች፣ የምርምርና ትብብር ፣ የአስተዳደርና ልማት ዘርፎች እንዲሁም የማናጅመንት ድጋፍ ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ቁልፍ የውጤት አመላካቾች ፣ የመደበኛና የሪፎርም ሥራዎች አፈጻጸም ሪፖርት በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የኢሲሰዩ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ በግምገማው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የግምግማ መድረኩ በዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ዕቅድ የተወሰዱና በመደበኛነት የታቀዱ ፣ በስምንት ስትራቴጂያዊ ግቦች ስር የተደራጁ ሁለት መቶ ሃያ ስምንት የሆኑ በዩኒቨርሲቲው የስራ ክፍሎች በጋራና በተናጠል ለመስራት የታቀዱ ቁልፍና ዝርዝር ተግባራትን የያዘውን መደበኛ ዕቅድ እንዲሁም ከኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተፈረመው የአፈጻጸም ኮንትራት ላይ የተመላከቱና በአምስት አውዶች የተቀመጡ ሰማንያ ቁልፍ የውጤት አመላካቾችን አስመልክቶ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራ የሚገመገሙበት፣ ሁለት መልከ ያለው መድረክ መሆኑ ከወትሮው የግምገማ መድረኮች ለየት እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡ ከኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተገባው ውል መሰረት የተካተቱት የውጤት አመላካቾችም አብዛኞቹ በዋናው ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ ሲሆኑ ሌሎች በተጨማሪነት የተሰጡ ተግባራት መኖራቸውን ያስታወሱት ፕ/ር ፍቅሬ የከፍተኛ ትምህርት ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ደረጃ የአፈጻጸም ቁልፍ አመላካቾች ሆነው የሚያገለግሉ ቁልፍ ተግባራትን የያዘ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ አክለውም በዩኒቨርሲቲው ቀጣይ ዕድገትና ለውጥ ሊያረጋግጡ የሚችሉ የሪፎርም ሥራዎችን በመከናወን ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ከእነዚህ የሪፎርም ሥራዎች መካከልም ወደ አዲስ አስተዳደራዊ ማዕቀፍ ማለትም ወደራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲነት ለመሸጋገር አስቻይ የሽግግር ሥራዎች በተለይም ፖሊሲዎችና ጋይድ ላይኖችን ማዘጋጀት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም በመጀመሪያ ደረጃ የአካዳሚክ ነጻነትን ሊያጎናጽፉ የሚችሉ ፖሊሲዎች መካከል የተማሪዎች ምልመላ፤ መረጣና ቅበላ ፖሊሲ፣ የምርምር ስራዎች የሚመሩበት አስተዳደራዊ ስራዓት፣ የትምህርትና ሥልጠና የውስጥ ኦዲት ፖሊሲዎች መዘጋጀታቸውን ለካውንስሉ አብራርተዋል፡፡
የትኩረት መስክ ልየታን በማስመልከትም የምርምር ዩኒቨርሲቲ የመሆን መስፈርቶቹን በሙሉ በማሟላት እና ዘመናዊና ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እንዲሁም ዲጂታል ዩኒቨርሲቲን ከመፍጠር አኳያ ብዙ ሥራዎች መሰራት እንደሚገባቸውና እስካሁንም በመሰራት ላይ ያሉትን ከሚቀርቡት ሪፖርቶች በመነሳት የሚገኙበትን የአፈጻጸም ደረጃ በአግባቡ መገምምገም አስፈላጊ መሆኑን አመላክተው የዕቅድ አፈጻጸሙም በባህሪው ሶስት መልክ ያለው ማለትም የተከናወኑ ተግባራት፣ ተጀምረው በሂደት ላይ ያሉ ተግባራት እና በባህሪያቸው በስድስት ወራት ውጤት የማይታይባቸው ተግባራት በመኖራቸው የካውንስሉ አባላት እነዚህን ባህሪያት በውል በመገንዘብ፣ ዕቅዱንና በመከናወን ላይ ያሉትን ተግባራት አፈጻጸም በስፋትና በጥልጿቀት በመተቸት፣ የአፈጻጸሙን ደረጃ፣ ጥንካሬና ጉድለቶች በጥልቀት እንዲገመግሙ የካውንስል አባለቱን አሳስበዋል፡፡
በመቀጠልም የአካዳሚክ ጉዳዮች ዘርፍ ሪፖርት በዶ/ር ለማ ጉዲሳ፣ የምርምርና ትብብር ዘርፍ ሪፖርት በዶ/ር አለማየሁ ደበበ፣ የአስተዳደርና ልማት ዘርፍ ሪፖርት በዶ/ር ታዴዎስ ሜንታ እና የማናጅመንት ድጋፍ ዘርፍ ሪፖርት በዶ/ር አብርሃም ሐጎስ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ቁልፍ የውጤት አመላካቾች ፣ የመደበኛና የሪፎርም ሥራዎች አፈጻጸም ሪፖርት በዝርዝር ቀርቦ ካወንስሉ በስፋት ተወያይቶባቸዋል፡፡ በቀረቡት ሪፖርቶች መሰረትም በየዘርፎቹ የታቀዱት የመደበኛ የሪፎርም ሥራዎች ዕቅድ እንዲሁም የቁልፍ ውጤት አመላካች የአፈጻጸም ደረጃቸው በመልካም ደረጃ የሚገኝ መሆኑ የቀረበ ሲሆን በቀጣይም የተማላ አፈጻጸም እንዲኖር በቀሪዎቹ ስድስት ወራት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችም በካውንስሉ አባላት ሀሳብና አስተያት ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በማጠቃለያው ላይም በተቀመጠው መደበኛ እቅድም ሆነ በቁልፍ ውጤት አመላካቾቹ የተቀመጡት መመዘኛዎች ሊተገበሩ የሚችሉ፣ እንደተግዳሮት የሚነሱ ጉዳዮችም ከአቅም በላይ ያልሆኑ ሊፈጸሙ የሚችሉ መሆናቸውን በመገንዘብ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በጽናት መስራት፣ በቀሪው ግማሽ ዓመትም ለላቀ አፈጻጸም መነሳት ተገቢ መሆኑን ተገልጿል፡፡