የኢሲሰዩ ካውንስል የ2015ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አደረገ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የ2015 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ አካሄደ፡፡ በግምገማው ላይም የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች እና በዩኒቨርሲቲው አዲስ የተካሄደው መዋቅራዊ አደረጃጀትን ተከትሎ በአመራር መደቦች ላይ የተመደቡ አዳዲስና ነባር የካውንስል አባላት ተሳትፈዋል፡፡
በስብሰባው መክፈቻ ላይ ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት አዳዲስ ለካውንስሉ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትና የመልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ያላቸውን ምኞት በመግለጽ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የ2015ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው በርካታ ስራዎችን የተከናወነበት ጥሩ ውጤቶችም የተመዘገቡበትና የተለያዩ ክስተቶችም የተከናወኑበት ዓመት እንደሆነ ለካውንስሉ አባላት ገልጸዋል፡፡ ለአብነት ያህልም በ2015 ዓ.ም የስራ ዘመን በትምህርት ዘርፉ ከተከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል ዩኒቨርሲቲው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰጠው የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና ለማዘጋጀት በማዕከልነት ተመርጦ፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ምሁራን በዩኒቨርሲቲው በመገኘት የመውጫ ፈተናውን በስኬት ማዘጋጀት የተቻለ ሲሆን በዚህም ስለዩኒቨርሲቲው በበርካታ ምሁራን ዘንድ ጥሩ የሆነ ግንዛቤ እንዲያዝ ከማስቻሉም ባሻገር ዩኒቨርሲቲውም ገቢ ማመንጨት መቻሉን እንዲሁም የተከታታይ ትምህርቱንም የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ሁለት ማዕከላትን በወሊሶና በለገጣፎ ከተሞች በመክፍት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ፕ/ር ፍቅሬ የገለጹ ሲሆን በዚህ አመትም በዩኒቨረሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር የሆነውን 2600 ተማሪዎችን በሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም የሚያስመርቅ መሆኑንና የቅበላ አቅሙንም ለማሳደግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ስራዎች መሰራታቸውን ለካውንስሉ አባላት ገልጸዋል፡፡
ፕ/ር ፍቅሬ አክለውም በርካታ የምርምር ስራዎችም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሰሩ መሆናቸውንና በትብብርና ትስስር በኩልም ከተለያዩ ኤንባሲዎችና አንባሳደሮች ጋር ዉይይት የተካሄደ ሲሆን ለአብነት ከአሜሪካ ኤንባሲ፣ ከሩሲያ አምባሳደር፣ ከኖርዌይ አምባሳደር እና ከሌሎችም ጋር በመወያየት ከኤንባሲዎቹና ከሀገራቸው ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር ስራዎች የተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በስትራቴጂያዊ ግቡ ባስቀመጠው መሰረትም የክረምት የሲቪል ሰርቫንት የወጣቶች ስልጠናና ፕሮግራምን በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱንና የተለያዩ የውስጥ ገቢን የሚያሳድጉ ስራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ፕ/ር ፍቅሬ ዩኒቨርሲቲው ለሰራተኞቹ ያሰራቸውን 175 እማወራና አባወራ የሚይዙ ዘመናዊ አፓርትማ የመኖሪያ ቤት ለእድለኞች ማስተላለፍ የተቻለበት እንዲሁም ዝቅተኛ ደምወዝ ተከፋይ ለሆኑ የተቋሙ ሰራተኞችም 20 ሼዶች ተሰርተው የተላለፉበት ዓመት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩልም በበጀት ዓመቱም እንደ የሴኔት ለጅስሌሽን ማሻሻያ ፣የክፍያ ስርዓት ማሻሻያ እና ሌሎችንም መመሪያዎችን የማሻሻልና ስራዎችን የበለጠ ለማቀላጠፍ የሚስችሉ መመሪዎችን የማዘጋጀትና የመከለስ ስራዎች የተከናወኑበት ዓመት ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዩኒቨርሲቲ ምድብ መካተቱን ተከትሎም አዲስ መዋቅር ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራዉ የተገባ በመሆኑ በተለያዩ የሀላፊነት መደቦች ላይ ሀላፊዎች የተመደቡ እና የመዋቅርና የድልድል ስራዉም በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለጹት ፕ/ር ፍቅሬ ካለው የዋጋ ግሽበት ጋር ለተማሪዎች ምግብ የሚሆን ግብዐት በጅት እጥረት፣ የነዳጅ፣ የትራንስፖርት እና ሌሎችም ችግሮችም ዩኒቨርሲቲውን የፈተኑበት ዓመት እንደነበርም ለካውንስሉ አስረድተዋል፡፡
በመቀጠልም የዘርፍ ሀላፊዎት የየዘርፋቸውን ክንውን ዝርዝር ሪፖረት ለካውንስሉ አቅርበዋል፡፡ በየዘርፉ በቀረበው ዝርዝር ሪፖርት ላይም የካውንስሉ አባላት የተለያዩ ሀሳብና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን በቀረቡት አሳብና አስታየቶችም ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በግምገማው ማጠቃለያ ላይም ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ እንደገለጹት በአጠቃላይ የበጀት ዓመቱ በርካታ ስራዎች የተሰሩበትና ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸው ለእቅድ አፈጻጸም ጥንካሬ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ አመራሮችና ሰራተኞች ምስጋናቸዉን አቀርበዋል ፡፡ በተጨማሪም በ2016 ዓ.ም በተሻለ እሳቤ እንደ ምርምር ዩኒርሲርቲ ልቆ ለመውጣት ከወዲሁ በቁርጠኝነት በጋራ መነሳት ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል፡፡