የኢሲሰዩ ካውንስል የ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ ክንውን ግምገማ አካሄደ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ ክንውን ግምገማ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ አካሄደ፡፡
በስብሰባው መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ዩኒቨርሲቲው ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ተጠሪነቱ ለኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር መሆኑን ተከትሎ በርካታ የሪፎርምና የማሻሻያ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ ባደረግነውም ጥረት ከአንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በምርምር ዩኒቨርሲቲ ምድብ ስር ለመመደብ የቻልን ቢሆንም ካሉት መስፈርቶችም መካከልም ገና በስፋት ልንሰራባቸው የሚገቡ መስፈርቶችን ከዕቅዱ ጋር ተካተው እየተተገበሩ መሆናቸውን የምንገመግምበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡ በመቀጠልም አሁን በመተግበር ላይ ባለው አዲስ የመዋቅር ለውጥ ጋር ታያይዞም አመራሩን የማደራጀት፣ ቀጥሎም የዩኒቨርሲቲውን የአካዳሚክ ዘርፍ አመራሮችን የመደልደል እንዲሁም የአስተዳደር ሰራተኞችንም በውድድር የመመደብ ሰፊ ስራዎችን ተሰርተዋል፤ የተቀሩትንም ለመመደብ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ የመዋቅር ለውጡን ተከትሎም የተለያዩ መመሪያዎች፣ ደንቦች እና ፖሊሲዎች ላይ የክለሳና የማሻሻል ስራዎች መሰራታቸውንና ከእነዚህ ክለሳ ከተደረገባቸው መመሪያዎች መካከልም የዩኒቨርሲቲው የሴኔት ሌጅስሌሽን በቅርቡ እንደሚጸድቅ ለካውንስሉ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ከተማሪዎች የመውጫ ፈተና እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በመተግበር ላይ ካለው ከድህረ ምረቃ የተማሪዎች ቅበላ ፈተናን ከአሁኑ ታሳቢ በማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ ለካውንስሉ አሳስበዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሥራም በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግና ሌሎች ተጓዳኝ ተግባራትም ላይ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ያመላከቱት ፕ/ር ፍቅሬ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ሁለትና ሶስት ዓመታት ውስጥ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን የተቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ ዩኒቨርሲቲው ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እንዲኖረው፣ ተመራጭ የሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲኖሩትና ተወዳዳሪ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን፣ በምርምር ዘርፉም ምርታማና ፋይዳ ያላቸው የምርምር ስራዎች የሚሰሩበት ስርዓት እንዲኖር ከወዲሁ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በግምገማው ላይም የአካዳሚክ ጉዳዮች ዘርፍ፣ የምርምርና ትብብር ዘርፍ፣ የአስተዳደርና ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚደንቶች ዶ/ር ለማ ጉዲሳ፣ ዶ/ር አለማየሁ ደበበ፣ ዶ/ር ታዲዎስ ሜንታ የየዘርፋቸውን የ 2016 ዓ.ም ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን የማኔጅመንት ድጋፍ ዘርፍ ሪፖርት ደግሞ በዶ/ር አብርሃም ሐጎስ የፕሬዚደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ቀርቦ ካውንስሉ በስፋት ተወያይቶበታል፡፡
በመጨረሻም ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ በሰጡት ማጠቃለያ አዲስ እየተተገበረ ያለው ሪፎርም ለዩኒቨርሲቲው እጅግ ወሳኝ ከመሆኑ አንጻር ሁሉም የስራ ክፍል የሪፎርም አጀንዳዎቹን በዕቅድ ውስጥ በማካተት ለተግባራዊነቱ መስራት ተገቢ መሆኑን በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዩኒቨርስቲ ምድብ ሥር የተካተተ መሆኑን በማስታወስ አንድ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶች አንጸር የበለጠ ብቁ ሆኖ መገኘት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው እዚህ ብቃት ላይ እንዲደርስ መስፈርቶቹን መሰረት በማድረግ በበለጠ ትጋትና ኃላፊነት መስራት ፣ ለዚህም ከአሁኑ መነሳት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡