የኢሲሰዩ ካውንስል የ2017 ዓ/ም የሶስተኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና በቀጣይ የሪፎርም ስራዎች አቅጣጫ ላይ ውይይት አደረገ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (ኢሲሰዩ) ካውንስል ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በህዳሴ አዳራሽ ባካሄደው ሶስተኛ መደበኛ የካዉንስል ስብሰባ የ2017 በጀት ዓመት የሶስተኛው ሩበ ዓመት የመደበኛና የሪፎርም ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ እና በቀጣይ የሚተገበሩ የሪፎርም አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሄደ፡፡
የውይይት መድረኩን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የኢሲሰዩ ፕሬዚደንት ዶ/ር ንጉሥ ታደሰ እንደተናገሩት በዚህ የሶስተኛ ሩብ ዓመት ግምገማ በዋናነት የሩብ ዓመት የመደበኛና የሪፎርም ሥራዎች ሪፖርት መገምገም እና በቀጣይ ዩኒቨርስቲዉ ሊያሻግር የሚችል ‘ግሎባል ሰታንድርድ’ ያለዉ ተቋም የማድረግ ሂደት ዉስጥ በሚኖረው የሪፎርም አፈጻጸም ፍኖተ ካርታ ላይ አቅጣጫ ማስቀመጥ እና መወያየት ፣ የጋራ ግንዛቤ መያዝ እና ለትገበራዉ ዝግጁ መሆን የሚሉት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡በሚቀጥሉት ጊዚያት በዋናነት ተቋሙ በሚሰጣቸዉ የትምህርት፣የምርምር እና የስልጠና ፕሮግራሞችን ማዘመንና ብሎም ወቅቱ ከሚጠይቀው ነባራዊ ሁኔታ መሄድ አማራጭ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ በሚፈለገዉ ቁመና ላይ ለመገኘት የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎችን መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ትግበራ ሁሉም የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አሻራዉን ማሳረፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በማስከተልም የሶስተኛው ሩበ ዓመት የመደበኛና የሪፎርም ሥራዎች አፈጻጸም ሪፖርት በስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ በሆኑት በአቶ ተፈሪ ጊሼ የቀረበ ሲሆን በሪፖርታቸው የዩኒቨርሲቲውን ስትራቴጂክ ግቦች ለማሳካት የተሰሩ ዝርዝር ተግባራትና ተቋሙ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተፈራረማቸውን ቁልፍ የውጤት አመላካቾች አተገባበር ላይ የተሰሩ ስራዎችን በዝርዝር ተግባራት አመላክተዋል፤ በትግበራዊ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና ለወደፊት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችንም ጠቁመዋል፡፡ በቀረበው ሪፖርት መሰረት ከካዉንስል አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የየዘርፍ አመራሮች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቀጣይም የኢሲሰዩ ፕሬዚደንት ዶ/ር ንጉሥ በተነሱ ሀሳቦች እና ጥያቄዎች ዘርዘር ያለ ማብራርያእና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡የዩኒቨርሲቲውን ልየታ በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች የተቋቋመዉ ኮሚቴ በሚያቀርበዉ ሀሳብ መሰረት የሚወሰን መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ አያይዘውም ተቋሙን ዘመናዊ እና አለምዓቀፍ ስታንዳርድ ያለዉ የስልጠና ተቋም፣ የተመረጡ የአካዳሚክ ፕሮግራሞችን የያዘ፣ ከፍ ያለ ብቃት ያለው አመራር እና ተመራጭ ባለሙያዎችን የምናፈራበት ተቋም ፣ ብሎም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወክል ተቋም ማድረግ ዋንኛ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ትግበራ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ማስቀደም የሚገባው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን ገልጸዉ ለዚህም መሳካት ከዩኒቨርስዉ ማህበረስብ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋ፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ በቀጣይ መሰራት ስላለባቸው ስራዎች አቅጣጫ የሰጡት ዶ/ር ንጉስ በጥልቀት መነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ እንቅስቃሴው ማስቀደም የሚገባው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን በመግለጽ አራት አጀንዳዎች ላይ ግን የበለጠ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡
ከእነዚህ አጀንዳዎች መካከልም የመጀመሪያው በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ሪፎርም በማድረግ እና ተቋሙን እንደገና በማዋቀር፣ የመማር ማስተማር፣ የምርምር፣ የስልጠና የማማከር እንዲሁም የአስተዳደር ስራዎችን እንደገና በመፈተሸ፤ ሁሉን አቀፍ የሆነ ተቋሙን የማደስ ስራ መስራት መሆኑን አብራርተው ተቋሙን እንደገና የማዋቀሩ ስራ ከተልዕኮ እና ከትኩረት አንጻር የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የቀረበውም በዩኒቨርሲቲው የተጀመሩት ሁሉንም ስራዎች በታቀዱት መሰረት በተገቢው ሁኔታ ማጠናቀቅ ፣ ሶስተኛው ተግባርም ዩኒቨርሲቲው የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በብሄራዊ ደረጃ እያካሄደ ላለው የሪፎርም ስራ የሚጠበቅበትን በመለየት በባለቤትነት መንፈስ በጋራ የመስራት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፤ በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው ደግሞ በተቋሙ የሚታዩ አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለተልዕኮው ስኬት ከልብ እንዲሰራ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በዕለቱ የቀረበው ሪፖርት በካውንስሉ በማጽደቅ ቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ሶስተኛዉ የካዉንስሉ መደበኛ ስብሰባ ተጠናቋል፡፡