የኢሲሰዩ ዘመናዊ መዋዕለ ሕጻናት በማስገንባት ለወሊሶ መስተዳደር አስረከበ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ሸዋ ዞን በወሊሶ ካምፓስ ያስገነባዉን ደረጃውን የጠበቀ ለመዋዕለ ሕጻናት አገልግሎት የሚውል ህንጻ ለከተማ አስተዳደሩ ጥቅምት 17 /2016 ዓ.ም የዩኒቨርስቲዉ ፕሬዚዳንት፣የቦርድ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌ ፣የአካባቢዉ ነዋሪዎች እና የወሊሶ ከተማ አስተደዳር ከንቲባ በተገኙበት ለወሊሶ ከተማ ትምህርት ቢሮ የቁልፍ ርክክብ አደረገ፡፡
በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ እንደተናገሩት የዩንቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ የመዋዕለ ህጻናቱን የግንባታ ሂደት ከጅምሩ ጀምሮ በልዩ ሁኔታ እና በአካል ቦታው ላይ በመገኘት ጭምር ሲከታተለው የቆየ ሲሆን በተደረገው ክትትልም የግንባታ ሂደቱ በታቀደው ሁኔታ ተጠናቆ ለዚህች እለት በመድረሳችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዉ በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቱ የተለያዩ ማህበረሰብ ተኮር ሥራዎችን እየሠራ እና በርካታ የአካባቢው የማህበረሰብ አባላትን ተጠቃሚ እያደረገ ሲሆን ነገር ግን ዩኒቨርሲቲዉ እስከ አሁን ካከናወናቸዉ የማህበረሰብ አገልግሎት ትልቁ እና በአጭር ግዜ የተጠናቀቀ ፕሮጀክት በመሆኑ በዚህ ፕሮጀክት ለተሳተፋችሁ በሙሉ ኃላፊነታችሁን በአግባቡ ስለተወጣችሁ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዉ የትምህርት ማዕከሉን መገንባት ብቻ ሳይሆን ለሕጻናቱ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ማለትም ወንበር ፣ጠረፔዛ፣ ለመኝታ የሚያገለግል ክፍል ከነቁሳቁሱ ጭምር ያዘጋጀ ሲሆን የተገነቡት ክፍሎች እና ቁሳቁሶች ደረጃቸዉን የጠበቁ ናቸዉ ብለዋል፡፡ወደፊትም ዩንቨርሲቲዉ ከማህበረሰቡ ጎን በመሆን ተቋማዊ ሀላፊቱን እንደሚወጣ ቃል ገብተዋል፡፡
የመስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ እንደገለጹት መዋዕለ ሕጻናት ት/ቤቱ እንደከተማ ብቻም ሳይሆን እንደክልልም በጥራት በአንደኛ ደረጃ የሚቀመጥ መዋዕለ ሕጻናት መሆኑን በመግለጽ ዩኒቨርስቲዉ በትዉልድ ግናባታ ሂደቱ የራሱን አሻራ አስቀምጧል ብለዋል ፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርስቲዉ ለትምህርት አጋዥ የሆኑ ቁሳቁስ ጭምር በማሟላት ስላስረከበን ምስጋናችን የላቀ ነዉ በማለት ለተደረገላቸዉ ትልቅ እገዛ በመስተዳደሩ ስም አመስግነዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች ለተደረገዉ ትልቅ ስራ ምስጋና በማቅረብ ለዘመናት ሲጠየቅ የነበረ ጥያቄ ዩኒቨርሲቲዉ በአጭር ግዜ በመመለሱ ያላቸዉን አክብሮት በምርቃት ገልፀዋል፡፡ በማስከተልም በዚህ ስራ ትልቅ አበርክቶ ላደረጉት ለዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ እና የማናጅመንት አባላት የክብር ሽልማት ሸልመዋል፡