የኢሲሰዩ የዓለም አቀፍ የፀረ- ሙስና ቀን አከበረ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ 18ኛ ጊዜ የሚከበረዉን የፀረ- ሙስና ቀን ‹‹ሙስናን መታገል በተግባር›› በሚል መሪ ቃል ህዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲዉ ህዳሴ አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች አከበሩ፡፡
በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ እንዳሉት ይህን ቀን ስናከበር በዋናነት ቀኑን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን ሙስና የሚያስከትለዉን ጉዳት በመገንዘብ ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን መጠየፍ በተጨማሪም በተግባር መታገል ያስፈልጋል፤ ለዚህም በተቋማችን ለምናደርገዉ የጸረ ሙስና ትግሎች በንቃት በመሳተፍ እያንዳንዳችን ጉልህ ድርሻ መወጣት አለብን ብለዋል፡፡ አመራሩ በምንም አይነት ሁኔታ ሙስናን እያየ የሚያልፍበት አካሄድ እንደሌለ በመግልጽ በቅርቡም በተቋሙ ያለአግባብ ያልተገባ ጥቅም ሲወስዱ የተገኙ ሰራተኞች ከስራ ማሰናበቱን ገልጸዋል፡፡ይህ ተግባር ወደፊት የሚቀጥል ሲሆን አመራሩ እና ሰራተኛዉ ብልሹ አሰራር እንዳይታገስ በጸረ ሙስና ትግሉም ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን አበክረዉ አሳስበዋል፡፡
በእለቱም በዶ/ር አለማየሁ ደበበ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ሙስናን መታገል በተግባር በሚል ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን በጽሁፉም ላይ ጠለቅ ያለ ዉይይት ተካሂዷል፡፡ በማስከተልም ‹‹የሙስና ተጋላጭነት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት›› በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሁፍ በዶ/ር ብርሀኑ በላይነህ የቀረበ ሲሆን ተሳታፊዉች በቀረበዉ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ዉይይት አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ሰፋ ያለ ማብራርያና ምላሽ የሰጡ ሲሆን በአጠቃላይ ሙስና ከመታገል አንጻር በ2015 ዓ.ም በተቋሙ ሊሰሩ የታቀዱ ዋና ዋና ስራዎች በዩኒቨርሲቲዉ የስነምግባርና ጸረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላም ተ/ሚካኤል ማብራርያ ተሰጥቶበታል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ ዳይሬክተሯ ለስራ ሂደቱ ከፍተኛ አመራሩ እያሳየ ያለዉን ድጋፍ በማመስገን ወደፊትም አመራሩ ድጋፍን እንዳያቋርጥ በማሳሰብ የእለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡