የኢሲሰዩ ፕሬዚዳንት ከአስተዳደር ዘርፍና ከማናጅመንት ድጋፍ ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር ተወያዩ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉሥ ታደሰ ከአስተዳደር ዘርፍና ከማናጅመንት ድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ከሚገኙ ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም በሴኔት አዳራሽ የትውውቅና የውይይት መድረክ አካሄዱ፡፡ በውይይት መድረኩ ላይም የየዘርፉ ኃላፊዎች እያከናወኗቸው ያሉትን ዓበይት ተግባራትና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ለፕሬዚደንቱ አቅርበዋል፡፡
በአስተዳደር ዘርፉ እየተተገበሩ ያሉ ክንውኖችን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት የአስተዳደርና ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ታዴዎስ ሜንታ ዘርፉ ከፕሬዚደንት ጽ/ቤት ጋር የተፈራረማቸውንና በየደረጃው ለስራ ክፍሎችና ቡድኖች የወረደው ቁልፍ የውጤት አመላካቾችን በአግባቡ ለመፈጸም በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መካከልም የተማሪዎች የምግብ በጀት፣ የመኪና እጥረት፣ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት፣ በአንዳንድ የሥራ ክፍሎች ከፍተኛ የሆነ የሰራተኞች እጥረት መኖር እና የመሳሰሉት ለተቋሙ ስኬት ወሳኝ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በገለጻቸው አመላክተዋል፡፡
የማናጅመንት ድጋፍ ዘርፍ የስራ ክንውንን የቀረቡት ዶ/ር አብርሃም ሐጎስ የፕሬዚደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ሲሆኑ በዘርፉ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው ዘርፉ የሪፎርም ሥራዎች ላይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የሶስት ዓመት የራስ-ገዝነት የሽግግር ስራዎችን ለይቶ እየሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ የራስ-ገዝነት የሽግግር ስራዎችን በተጨማሪም ቁልፍ የውጤት አመላካቾች አስመልክተውም የተከናወኑ እና በጥሩ የክንውን ሂደት ላይ ያሉ አመላካቾች መኖራቸውን ጠቁመው በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ በአንዳንድ የሥራ ክፍሎች የሚታይ የሰው ኃልይ እጥረት፣ አስፈላጊ የሆኑ የግብአቶች እጥረት፣ የተጠናቀቁ የራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ የሽግግር ፖሊሲ ሰነዶችላይ የቋንቋ የአርትኦት ሥራ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚደረግ አውደ-ጥናት ዝግጅት፣ እየተከናወኑ በሚገኙ ቁልፍ የውጤት አመላካቾች አተገባበር ላይ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣ በሚዲያ ሽፋን ማግኘትና ድረ-ገጽን ማዘመን እና ሌሎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ዶ/ር አብርሀም ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ በተቋሙ በመሰራት ላይ ያሉ በርካታ መልካም ተግባራትን ማስቀጠል እና አዳዲስ አሰራሮች መተግበር፤ በቀጣይ ይህ ተቋም አሁን ካለበት ደረጃ የበለጠ እንዴት መጠናከር እንዳለበት በጥልቀት ማጤን እና ለውጤታማነቱም በትጋት መንቀሳቀስ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በየዘርፎቹ እንዲሁም በስራ አስፈጻሚዎች ለተነሱት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችም እንደየቅደም ተከተላቸውና አንገብጋቢነታቸው እየተለዩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሰሩት በማኔጅመንት እየተለዩ ካለው በጀትና ጊዜ ጋር እየታዩ በሂደት እየተፈቱ የሚሄዱ መሆናቸውን፣ ነገር ግን ሁሉም ችግር በአንድ ጊዜ ሊፈታ እንደማይችል አመላክተዋል፡፡ ቁልፍ የውጤት አመላካቾችን አስመልክቶም መረጃዎች በአግባቡ መሰነድና መደራጀት እንዳለባቸውና በአግባቡ ሪፖርት መደረግ እንደሚገባቸው፣ በስትራቴጂያዊ ትብብርና አጋርነትም ላይ በስፋትና በጥልቀት መሰራት እንዳለበት በተጨማሪም በቀጣይ በሚከናወኑ የለዉጥ ስራዎች ሁሉም የዩንቨርስቲዉ ማህበረሰብ በባለቤትነት እና በእኔነት ስሜት መሳተፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡