የኢሲሰዩ ፕሬዚዳንት የዩኒቨርሲቲዉን የተለያዩ የስራ ክፍሎች ጎበኙ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉሥ ታደሰ በዩኒቨርሲቲዉ የሚገኙ ኮሌጆች ፣ትምህርት ክፍሎች እና የተለያዩ የስራ ክፍሎች መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም ጎበኙ፡፡
በሁለተኛ ዙር የተቋም ጉብኝታቸዉ በአካዳሚክ ዘርፍ የተደራጁ የስልጠና ኢንስቲቲዩት፣የፋይናንስ፣ ልማትና ማኔጅመንት ኮሌጅ፣የአመራርና አስተዳደር ኮሌጅ፣የሕግ ትምህርት ቤት፣ ዋና ሬጅስትራር ሲጎበኙ ከየኮሌጆቹ ዲኖች እና ምክትል ዲኖች እንዲሁም የትምህር ክፍል ሃላፊዎች ጋር ተዋዉቀዋል፤ ሀላፊዎቹም ያሉ ነበራዊ ሁኔታዎችን ያብራሩላቸዉ ሲሆን እንደስራ ክፍል የሚያስፈልጉ የግብአት ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
በምርምር ዘርፍ በተደረገ የስራ ክፍሎች ጉብኝት ምርምርና ማማከር ማዕከላት ዳይሬክቶሬት፣ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ማህበረሰብ አሳታፊነት፣ ኢንዱስተሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት፣ የአበልጽጎት ማዕከል እና ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ጎብኝተዋል በዚህም ከሃላፊዎች ጋር ዉይይት ያደረጉ ሲሆን በቅርቡ የተጠናቀቀዉን ዘመናዊ ኪችን እና የአካዳሚክ ህንጻ ጎብኝተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በተለይ ሁኔታ ወደፊት ለሚተገበሩ የሪፎርም ስራዎች ያሉት ፋሲሊቲዎች ለስራዎች አቅም እንደሚሆኑ በመግለጽል ፣ ፋሲሊቲዎችን የማዘመን ስራ እና ለተቋቋመበት ዓላማ በጥራት እና በብቃት ማዋል ላይ በአመራሩ በኩል ትልቅ ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ የሽፋን ሂደት በማሻሻል ተደራሽነቱን ለማስፋት ፐብሊክ ሴክተሩን ያማከሉ ፕሮግራሞች ቀረጻ ላይ ጣቢያዉ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደረግ በማሳሰብ ያሉት ችግሮች በአጭር ግዜ እንደሚቀረፍ ገልጸዋል፡፡የምርምር እና ትብብር ዘርፍ ግራንት ማፈላለግና ትብብር በልዩ ሁኔታ ሊጠናከር እንደሚገባ እና ለተቋሙም ትልቅ አቅም መሆን አለበት ብለዋል፡፡ መማሪያ ክፍሎች በተመለከተ ዘመናዊ ለማድረግ ወደፊት ትልቅ ስራ እንደሚጠይቅ ገልጸዉ በተለይ በሚቀጠለዉ በጀት አመት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠዉ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በዚህ በሁለት ዙር ባደረጉት ጉብኝት ስለ ተቋሙ አሰራር እና ፋሲሊቲዎች ሙሉ ግንዛቤ እንዳገኙ በመግለጽ በቀጣይ ከአካዳሚክ እና አስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች ጋር ትዉዉቅ እና ዉይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡