የኢትዮጲያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ሆነዉ ሲያገለግሉ የቆዩት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ አዲስ ለተመደቡት ፕሬዚዳንት ለ ዶ/ር ንጉሥ ታደሰ ርክክብ አደረጉ
የኢትዮጲያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ሆነዉ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲያገለግሉ የቆዩት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ከየካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጲያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ሆነዉ ለተሾሙት ለ ዶ/ር ንጉሥ ታደሰ ርክክብ አደረጉ፡፡
የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም በተደረገው የስራ ርክክብ ወቅት ፕ/ር ፍቅሬ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ያሉትና በቀጣይም በአዲሱ አመራር ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ያሏቸውን አንኳር ጉዳዮች ባጭሩ አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት ሪፖርትም ዩኒቨርሲቲው በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በፈጸመው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት ዩኒቨርሲቲው የተቀበላቸውን ቁልፍ የውጤት አመላካቾች በተቋሙ በየደረጃው እስከ ቡድን መሪ ድረስ የወረዱ መሆናቸውን፣ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በሚደረገው ጥረትም የተለያዩ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ተዘጋጅተው የተጠናቀቁና በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በተሰጠው ተልዕኮ መሰረትም በመደበኛነት ከሚሰጠው የትምህርት መርሀ ግብር በተጨማሪ የሰው ሀብት ልማት ላይ ያተኮረ የብቃት ማጎልበቻና ምዘና ኢኒስትቲዩት በመቋቋም ላይ መሆኑን በሪፖርታቸው ያመላከቱ ሲሆን ሁለት ትልልቅ አዳዲስ ባለ ስምንት ወለል እና ባለ ሰባት ወለል የግንባታ ፕሮጀክቶች ፣ በወሊሶ ካምፓስም አዳዲስና ነባር ፐሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የምርምርና የስልጠና ፕሮጀክቶች ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር በውል ስምምነት ተይዘው እየተሰሩ መሆናቸውን፣ የዩኒቨርሲቲው የበጀት አፈጻጸምም ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደሆነ እና በእስካሁኑ ሂደትም ዩኒቨርስቲው በየጊዜው የሚመደብለትን በጀት በአግባቡ በጥቅም ላይ የሚያውል ተቋም መሆኑ የገለጹት ፕ/ር ፍቅሬ በተቋሙ ሌሎችም ሰፋፊ ሥራዎችም እየተሰሩ መሆናቸውን፣ ዩኒቨርሲቲውም ማንኛው ማህበረሰብ ክፍል ያለ ምንም የፖለቲካ ወገንተኝነት ገብቶ የሚማርበት፣ ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን መቻሉን አመላክተዋል፡፡ ፕ/ር ፍቅሬ አክለውም በዩኒቨርሲቲው ያለው አመራርና ሰራተኛም እጅግ በጣም ታታሪ የሆነ እና በጥሩ የስራ መንፈስ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው ለአዲሱ አመራርም መልካም እና ውጤታማ የሆነ የሥራ ዘመን እንዲሆላቸው ያለቸውን መልካም ምኞት ገልጸዋል፡፡
አዲስ የተሾሙት ዶ/ር ንጉሥ ታደሰ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በጣም የተደራጀ ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ ለስራ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር የተረጋጋ ስፍራ በመሆኑ ወደ ዩኒቨርሲቲው በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ነባሩ አመራር ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ዩኒቨርሲቲውን አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የቻለ ሲሆን ያለውን ጠንካራ ጎን አጠናክረን ወደፊት መራመድ ይጠበቅብናል ያሉት ዶ/ር ንጉሥ ታደሰ በቀጣይ በየዘርፎች በሚቀርበው ሪፖርት መነሻነትም ምን መሻሻል እንደሚገባውና ምን ላይ የበለጠ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ የሚታይ መሆኑን ገልጸው ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ተቋሙን የበለጠ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡
-------------------
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች እና ሠራተኞች ለዶ/ር ንጉሥ ታደሰ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞት ይገልጻሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ