የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ከኢሲሰዩ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ጋር ተወያዩ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ጋር ቀጣይ የሚከናወኑ የምክክር መርሃ ግብር በኢሲሰዩ በሚካሄድበት ሁኔታ ላይ ውይይት አደረጉ፡፡
ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም በኢሲሰዩ ሴኔት አዳራሽ በተደረገው በዚህ ውይይት ላይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርአያ ባደረጉት ገለጻ በኮሚሽኑ እስከአሁን የተከናወኑ አቤት ክንዉኖች ላይ ገለጻ አድርገዋል ፡፡በዚህም መሰረት በአስር ክልሎች ላይ አጀንዳዎችን ለይቶ መጨረሱን እና ከቀሩት ሁለት ክልሎች ማለትም የአማራና የትግራይ ክልሎች መካከል በአማራ ክልል የአጀንዳ ልየታው የቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቀደም ብሎም በኦሮሚያ ክልል በተደረገው ውይይት በክልሉ ካሉት 356 ወረዳዎች ተሳታፊዎች በሙሉ አዳማ ላይ በማሰባሰብ በዉጤታማነተ የተጠናቀቀ መሆኑና በዚያው መሰረት በአማራ ክልልም በተመሳሳይ ሁኔታ ለማከናወንና ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልልም የሚገኙ 267 ወረዳዎችን በተለያዩ 4 ክላስተሮች ማለትም የባህርዳር ፣ ደሴ ፣ የጎንደር እና የደብረ ብርሃን ክላስተርን በማደራጀት የወረዳ ተሳታፊዎች መረጣ እየተካሄደ ይገኛል ብዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲም ለሚቀጥሉት የኮሚሽኑ የምክክር መርሀ ግብሮች ዝግጅት የተመረጠ በመሆኑ ለዚህ ታላቅ ተግባርና ኃላፊነት ባለው ልምድና ፋሲሊቲ ተመራጭ መሆኑን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ለሚመጡ ተወያዮች መርሀ ግብሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕ/ር ፍቅሬ ዳሳለኝ በበኩላቸው ለዚህ አላማ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በመመረጡ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ባለው የካበተ ልምድና ፋሲሊቲ ሀገራዊ ሀላፊነቱን እንደተቋምም እንደ ዜጋም የዩቨርሲቲዉ ማህበረሰብ ሀላፊነቱን እንደሚወጣ ለኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ተሳታፊዎች በዩኒቨርሲቲዉ በሚኖራቸው ቆይታ አስተማማኝ፣ዉጤታማና የተሳካ እንደሚሆን አብራርተዋል ፡፡