የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች በመደበኛ፣በክረምት፣ በኤክስቴንሽን መረሃ-ግብር ሲያስተምራቸው የቆዩ 180 በመጀመሪያ ዲግሪ 2186 በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም 11 በፒኤችዲ ዲግሪ በድመሩ 2377 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት ሐምሌ 15/2015ዓ.ም በዩኒቨርስቲዉ ዋና ግቢ አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ፣ የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባል እንዲሁም የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስተር ዲኤታ ጨምሮ የሴኔት አባላት፣ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
በምረቃው ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ተቋሙ ተወዳዳሪና ተመራጭ የድህረ ምረቃና ምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ከትምህርት ሚኒስቴር የተሰጡ የሪፎርም አቅጣጫዎችና በዩኒቨርሰቲው የተለዩ እስትራቴጂክ ግቦች መነሻ በማድረግ የተለያዩ ስራዎች እንደተሰሩ በመግለጽ ተቋሙ 2015 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ በአዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት ብቁ አመራር እንዲኖር በተሰራው ስራ በውድድር ላሸነፉ 74 የአካዳሚክና 47 የአስተዳደር አመራር መደቦች ላይ ምደባና ስመሪት መስጠት እንደተቻለ እና የባለሙያዎች ምደባም በቅርቡ እንደሚጠናቀቀ በመግለጽ መዋቅራዊዉን አደረጃጀት መሰረት በማድረግ የሴኔት መተዳደሪያ ደንብን ጨምሮ ሌሎች የውስጥ አሰራር ደንቦች፤ ፖሊሲዎች እና መመሪያዎችን ላይ የማሻሻያ ስራዎች እንደተሰራ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲዉ ባለፉት30ዓመታት የሲቪል ሰርቪሱን አቅም በመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ እና ይሄን ተግባሩን ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስበዋል ፡፡ ተመራቂዎችም ችግር ፈቺ ሥራዎችን በማከናወን የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ በማሳሰብ በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ ያካበታችሁትን እውቀት ለአገር ለውጥ እና ለሲቪል ሰርቪሱ ለዉጥ ማዋል አለባችሁ ብለዋል።
በምረቃው ላይ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር በማማከር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና በአካዳሚኩ ዘርፍ የተለያየ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ሚኒስቴር ሥር እንዲደራጅ በመወሰኑና በሀገራችን ካሉት አንጋፋና የመጀመሪያው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በድህረ ምረቃና ምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ምድብ መመደብ በመቻሉ የሀገሪቷን ሲቪል ሰርቪስ የማዘመን ተልዕኮውን በብቃት ለማከናወን ጠንካራ መንፈስና ተነሳሽነት እንዲፈጠር አስችሏል ብለዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች ለሕዝብ ጥቅምና ለአገራዊ ለውጥ በቅንነትና በታማኝነት ሊሰሩ ይገባል፤ በተጨማሪም ሌብነትን የሚጸየፍና ሥነ-ምግባር ያለው ሲቪል ሰርቫንት እንዲገነባ ምሩቃን የበኩላቸሁን ሚና መወጣት አለባቸሁ በማለት አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም ዩኒቨርስቲዉ የላቀ የድህረ ምረቃና የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ለሚደረገዉ ጥረት ትምህርት ሚኒስትር ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ ሲሆን የዩኒቨርሲቲዉ አመራሮችና ሰራተኞችም በዩኒቨርስቲዉ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች በሙሉ አቅም እንዲተገብሩ ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ እና የክብር እንግዳዉ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ለተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክቶቻቸውን በማስተላለፍ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የሜዳሊያ ሽልማት አበርክተዋል።