የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በወሊሶ ካምፓስ ያስገነባዉን መዋዕለ ሕጻናት ርክክብ ሊያደርግ ነው
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ሸዋ ዞን በወሊሶ ካምፓስ ያስገነባዉን ደረጃውን የጠበቀ ለመዋዕለ ሕጻናት አገልግሎት የሚውል ህንጻ ለከተማ አስተዳደሩ ርክክብ ሊያደርግ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በወሊሶ ከተማ በማስገንባት ላይ ካለው የወሊሶ ካምፓስ ግንባታ ጎን ለጎን በልዩ ትኩረት በማከናወን ላይ ባለው የማህበረሰብ አገልግሎት መሰረት ለአካባቢው ማህበረሰብ ልጆች የትምህርት አገልግሎት የሚውል የመዋዕለ ህጻናት ህንጻም ሲያስገነባ ቆይቷል፡፡ የዩንቨርስቲው የሥራ አመራር ቦርድም የመዋዕለ ህጻናቱን የግንባታ ሂደት ከጅምሩ ጀምሮ በልዩ ሁኔታ እና በአካል ቦታው ላይ በመገኘት ጭምር ሲከታተለው የቆየ ሲሆን በተደረገው ክትትልም የግንባታ ሂደቱ በታቀደው ሁኔታ ተጠናቆ ለ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራው ለማስጀመር ዝግጁ እንዲሆን ተደርጓል።
በዚህም ጥቅምት 17/2016 የዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በተገኙብት ከወሊሶ ከተማ አስተዳደር ጋር ርክክብ ያደርጋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በዋናው ካምፓስም በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቱ የተለያዩ ማህበረሰብ ተኮር ሥራዎችን እየሠራ እና በርካታ የአካባቢው የማህበረሰብ አባላትን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል።