የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የጥናት የማማከር ውል ስምምነት ሰነድ ከአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ጋር ተፈራረመ
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የኢንተርፕራይዞችን የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ገበያ ትስስር ውጤታማነትና ዘላቂነት ለማረጋገጥና ፀጋን ለመለየት የሚያስችል ጥናት የማማከር ውል ስምምነት ሰነድ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተፈራርሟል።
ኢንተርፕራይዞች የሚገጥማቸውን ችግር በጥናት በመለየት በጥናቱ ግኝት መሰረት አሰራርን በማሻሻል እና ለፖሊሲ ግብአት ከመጠቀም ባለፈ የመክሰም ምጣኔ በመቀነስ እና ዘላቂ የገበያ ትስስር በመፍጠር ሂደት የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ እንደሚያግዝ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጥራቱ በየነ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተቋማት ጋር የተለያዩ ጥናትና ምርምር ስራዎችን ማካሄዱን በማስታወስ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ጥናቱን ሰርቶ ለማስረከብ ከቢሮው ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ ከ24ሺ በላይ ኢንተርፕራይዞች እንደሚገኙ የተናገሩት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ የኢንተርፕራይዝና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድ ልጋኒ ጥናቱ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥሟቸውን የሀገር ውስጥ የውጭ ሀገር የገበያ ትስስር ችግር በመፍታት እንደ ሀገር አርዓያ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል
ምንጭ፡የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ