የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 2ሺህ 683 ተማሪዎችን አስመረቀ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 2ሺህ 683 ተማሪዎችን ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው አመራር፣ የፌደራል የስራ ኃላፋዎች፣ ባለድርሻ አካላትእና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዩኒቨርሲቲዉ ዋና ግቢ አስመረቀ ፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 654ቱ ሴቶች ተመራቂዎች ናቸዉ።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክብር እንግዳው ክቡር ዶ/ር ተመስገን ቡርቃ (የኢ.ሲ.ሰ.ዩ ቦርድ ሰብሳቢ) እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲዉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የመንግስትን ፖሊሲና ፕሮግራም አቅጣጫ በመከተል አሰራሩን እያሻሻለ፣ፕሮግራሞችን እያሰፋና የሲቪል ሰርቪሱን አቅም በመገንባት እነሆ ዘንድሮ 28 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ሁለት ፕሮግራሞችንና ጥቂት ተማሪዎችን ይዞ ውስን በሆነ መሰረተ ልማት በኮሌጅ ደረጃ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዩኒቨርሲቲያችን ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ ቢሆንም ድንቅ የሚባል ውጤትም በማስመዝገብ ላይ ይገኛል ብለዋል ፡፡ይህ ደግሞ የተሰጠውን የሲቪል ሰርቪሱን አቅም የመገንባት ተልእኮ በትምህርት፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት፣ በስልጠናና ማማከር ዘርፍ ትኩረት አድርጎ በመስራት የሲቪል ሰርቪሱን አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን በማከናወኑ ነዉ ብለዋል ፡፡ ተመራቂዎች በሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት እያንዳንዱን ማህበረሰብ በቀናነትና ታማኝነት በማገልገል የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች ልትሞሉ ይገባል ብለዋል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ዩኒቨርሲቲዉ የሀገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ዘርፍ የማዘመን ተግባር ላይ ጉልህ ድርሻ ስላለው ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው የቀሰማችሁትን እውቀት ከወትሮው በተሻለ ሀገራዊ ለውጥና እድገት የድርሻችሁን መወጣት አለባችሁ ብለዋል። ዩኒቨርሲቲያችን ተጠሪነት ለኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር እንዲሆን እና በተደረገው የአደረጃጀት ለውጥም ዩኒቨርሲቲው ከምስረታው ጀምሮ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች በጥልቀት በመመልከት በሀገሪቱ ካሉት አንጋፋና የመጀመሪያው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች(First Generation University) ጋር በምርምር ዩኒቨርሲቲ ምድብ መመደብ በመቻሉ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ያለው ትርጉም እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የሀገሪቷን ሲቪል ሰርቪስ የማዘመን ተልዕኮውን በብቃት ለማከናወን ጠንካራ መንፈስና ተነሳሽነት እንዲፈጠር አስችሏል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የዕለቱ የክብር እንግዳ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡት የተዘጋጀውን ሜዳሊያ በማበርከት የእለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡