የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 6ኛው የማህበረሰብ አገልግሎት እና የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያ ምስረታ ቀን አከበረ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 6ኛውን የማህበረሰብ አገልግሎት ቀን እና የሲቪል ሰርቪስ የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያ ኤፍ ኤም 100.5 የተመሰረተበትን 6ኛ ዓመት የተለያዩ መርሃ ግብሮች በማከናወን ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም በአባይ አዳራሽ አከበረ፡፡
በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አለማየሁ ደበበ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የፓናል ውይይት ተካፋዮች ወቅታዊ በሆነው የሀይማኖት ግጭት ላይ የድርሻቸውን ለማበርከት ውድ የሆነውን ጊዜያቸውን ሰውተው በመምጣታቸው ያላቸውን አክብሮት ገልፀው፤ አንዳችን ከአንዳችን ተለያይተን መኖር የማንችልበት መሆናችንን በመገንዘብ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን በጋራ በመፍታት ነገን የተሻለ ማድረግ እንችላለን ብለዋል፡፡
የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ተሾመ በበኩላቸው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ላለፉት 6 ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ ልማታዊና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ ለቀጣይም እነዚህን እንቅስቃሴዎች ከበፊት በተሻለ መልኩ በማጠናከር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች የሚሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት የሃይማኖት አባቶችን መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ እና ኡስታዝ አቡበከር አህመድን በመገኘት ወቅታዊ በሆነው በሀይማኖት ሽፋን በሚደረጉ የጥፋት እንቅስቃሴዎች ምን እልባት ማግኘት አለባቸው በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ አስተማሪ የሆኑ ሀሳቦችንና ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎችን ለበዓሉ ተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡
የፓናል ውይይት አቅራቢዎቹ እንዳሉት አሁን ያሉት ችግሮች የተፈጠሩት አብዛኛው ሰው ሁሉንም ነገር እንደወረደ እየተቀበለ እና የራሱን ፍላጎት ብቻ እያስቀደመ መሆኑኑ ጠቁመው ከምንም ነገር በፊት ሰው መሆንን ማስቀደም ተገቢ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ግጭቶች ቢኖሩም ችግሮችን ለመቅረፍ ጠንክሮ መሰራት እንደሚገባና በምድር ላይ መተን መልካም ነገርን መጨመር ካልቻልን እኛ እራሳችን ተጨማሪ ሸክም በመሆናችን በምድር ላይ ስንኖር አንድ እሴት የመጨመር ግዴታን ይዘን መምጣታቻችንን መዘንጋት የለብንም የሚል መልዕክትን አስተላልፈዋል፡፡ እንደዚህ አይነት የመወያያ መድረኮች ለውጥ ለማምጣት የሚጠቅሙ መሆናቸውን በመግለጽ ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት እንጂ ከተፈጠሩ በኃላ ለመነጋገር ከመቀመጥ ይልቅ ቀድሞ የማስቀረት ልምድ ማዳበር ተገቢ መሆኑምም አመልክተዋል፡፡
አስከትለውም ከበዓሉ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ሀሳቦችና አስተያየቶች በሁለቱም ተጋባዥ እንግዶች ሰፋ ያለ ማብራሪያዎች እና ምላሾችም ተሰጥተዋል፡፡
ከፓናል ውይይቱም በማስከተል በአዲስ አበባ የሚገኙ ታሪካዊ እና ጥንታዊ የሆኑ በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶች እና አብያተ ቤተ ክርስቲያናትን የሚያሳይ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ የተካሄደ ሲሆን አውደ ርዕዩም ለተጋበዥ እንግዶች፣ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንዲሁም ለተማሪዎች ለእይታ ክፍት እንዲሆን ተደርጓል፡፡