የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ኃብት ፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢሲሰዩ የመስክ ምልከታና ውይይት አደረገ፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም የመስክ ምልከታና ውይይት አካሄደ ፡፡ የመስክ ምልከታው ዓላማም በዩኒቨርሲቲው ያለው የመማር ማስተማር ስራ ያለበትን ደረጃ ማረጋገጥ ሲሆን በምልከታ ወቅትም ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የስራ ክፍሎች፣ ከመምህራንና የተማሪ ተወካዮች ጋር እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች ጋር የተናጠል ውይይቶችን አድርጓል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም በዩኒቨርሲቲው ያለውን መሰረተ ልማት፣ ፕሮጀክቶችንና ለመማር ማስተማር ስራው ወሳኝ የሆኑ ግባዓቶች ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎችና ለሰልጣኞች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ የሚያስገነዝብ ገለጻም ተደርጎላቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው ያደራጀውን የዳታ ሴንተር፣ ለስልጠናና ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚያገለግሉ ስማርት ክፍሎች፣ የምርምር አበልጽጎት ማዕከል፣ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ የግንባታ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በዝግጅት ላይ የሚገኘው የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና ዝግጅት እና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በጋራ እየተከናወነ ያለውን የመንግስት ሰራተኞት የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከል እንቅስቃሴን በስፋት ጎብኝተዋል፡፡
በዚህ በተጨማሪም ኮሚቴው ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ከመምህራንና የተማሪ ተወካዮች እንዲሁም ከአስተዳደር ሰራተኞች ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በስፋት ተወያይቷል፡፡ በውይይቱም የዩኒቨርሲቲውን የአመራር ሁኔታ፣ በመልካም አስተዳደርና ዙርያ የተሰሩ ሥራዎች፣የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመማር ማስተማር ሂደት ውጤታማነትን ለማሻሻል የታቀዱና የተሰሩ ሥራዎች፣ የጥናትና ምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትአሰጣጥና ሌሎች ተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተነሱት ጉዳዮች ላይም ኮሚቴው ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች ጋር በስፋት የተወያየባቸዉ ሲሆን አመራሩም ለተነሱ ማብራርያ ለሚሹ ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ ሰጥቶባቸዋል ፡፡