የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የመደበኛና የሪፎርም ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የመደበኛና የሪፎርም ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዳሴ አዳራሽ አካሄደ፡፡ በግምገማ መድረኩም የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ዕቅድ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖረት ላይ ካውንስሉ በዝርዝር ተወያይቷል፡፡
በግምገማ መድረኩም ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የቀረበው ዕቅድ የየዘርፍ አመራሮች የተሳተፉነትና በየደረጃው ሰፊ ውይይት ሲደረግበት የቆየ መሆኑን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የአስር ዓመት በስትራቴጂክ ዕቅድ የተቀመጡ ቁልፍ ተግባራትን፤ የዩኒቨርሲቲውን ቀጣይ ዕድገትና ለዉጥ ሊያረጋግጡ የሚችሉ የሪፎርም ስራዎችን ፤ በትምህርት ሚኒስቴር በዋናነት የትምህርትና ምርምር ስራዎች ጥራት ለማረጋገጥና ዲጅታል የትምህርት ስርዓት ለመዘርጋት የተሰጡ አቅጣጫዎች እንድሁም የእነዚህ ተግባራት አፈጻጸምን ለመለካት የተቀመጡ ዉጤት አመላካቾች መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ ዕቅድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተዘጋጀዉ ረቂቅ ዕቅድ በተለይም እያንዳንዱ ቁልፍ ተግባር ከተመደበው የዓመቱ በጀት አንጻር ምን ያህል ተጨባጭና ተፈጻሚ መሆን እንደሚችል ግምገማ ተደርጎ እና በማናጅመንት ካዉንስል ደረጃ የጸደቀ በመሆኑ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በትጋት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ወራት የሥራ ክንውንን አስመልክተውም የክረምትና ተከታታይ ትምህርት ሲሰጥ የቆየ መሆኑን፣ የብሔራው ፈተና ተፈታኞች ድጋፍ ማድረግ፣ የመምህርን አቅምን የመገንባት ስራዎች፣ የተለያዩ ስልጠናዎችና የምዘና አገልግሎት ለሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ሲሰጥ የቆየ መሆኑንና የ2027 ዓ.ም ተማሪዎችን የመመዝገብ እና የማስተማር ስራን ማጀመር በአካዳሚክ ዘርፍ መከናወናቸውን የጠቀሱት ፕ/ር ፍቅሬ በምርምር ዘርፉም ከመንግስት በተፈቀደ በጀት የሚሰሩ ምርምሮችን የመምረጥ እና በበጀት የመደገፍ፣ በሀገር ውስጥ ተቋም በተደረገ በጀት ድጋፍ የሚሰራ ምርምር ማካሄድና ማጠናቀቅ፤ የምርምር ውጤቶችን በጆርናሎችና ፕሮሲዲንግ በማሳተም ለተጠቃሚዎች ተደራሽ የሚሆኑበት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች፣ የምርምር ውጤቶችን በዲጂታል ቋት የማሰባሰብ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው እንዲሁም በአስተዳደርና ልማት እና በማኔጅመንት ድጋፍ ዘርፎችም ለራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲነት እየተደረገ ባለው ጥረት ዩኒቨርሲቲው ብቁና በቂ የአካዳሚክ ሠራተኞች እንዲኖሩት የአካዳሚክ ሰራተኞች ፕሮፋይል የማደራጀትና የመተንተን እንዲሁም አዲስ ዉል የማስገባት፤ የትምህርት አቅርቦቶችን የማሟላት፤ ፋሲሊቲዎች (ቢሮዎችን) የማደራጀትና አገልግሎት እንድሰጡ ማድረግ፤ የኮሪዶር ልማት አካል ሆኖ ከመንግስት በተፈቀደ 48 ሚሊዮን ብር በጀት የተጀመሩ የአጥር፤ የሴፕቲንክ ታንኮች ግንባታና እና የህንፃዎች እድሳት ማጠናቀቅ፤ የአዲስና ነባር የግንባታና የዉሃ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀምን የመከታተል፤ ክፍያዎችን መፈጸም፤ አዳዲስ የውስጥ ገቢ ማምንጫዎችን በግባኣት ማደራጀት፤ የ2016 በጀት ዓመት ሂሳብ ኦዲት ማስደረግ፤ ያለፉት በጀት ዓመታት ኦዲት ግኝቶችን በወሳኝነት የማጽዳት፤ ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በግዥ የማሟላት፤ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ተቋማት ጋር ትብብርና ትስስር ለመፍጠር የተደረጉ ጥረቶች እና መሰል ሰፋፊ ስራዎች ባለፉት ሶስት ወራት መከናወናቸውን ፕ/ር ፍቅሬ ለካውንስሉ ገልጸዋል፡፡
ከሪፎርም ዕቅድ አፈጻጸም አኳያም ዩኒቨርሲቲያችን ቀጣይነት ያለውን ዕድገትና ለውጥ ለማረጋገጥ ወደ አዲስ አስተዳደራዊ ማዕቀፍ ማለትም ወደ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲነት ለመሸጋገር ከ2016 ጀምሮ የሽግግር ሥራዎችን በዕቅድ ተይዘው ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ፖሊሲዎችና ጋይድላይን ማዘጋጀት፤ የተማሪዎች ምልመላ፣መረጣና ቅበላ ፖሊሲ፤ የምርምር ስራዎች የሚመሩበት አስተዳደራዊ ስርዓት ፤ የዉስጥ ጥራት ኦዲት ፖሊስ፤ ተመራጭ የሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞች የመቅረጽ፤ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ለመፍጠር አዳዲስ ገቢ ማስገቢያ ምንጮች በዳሰሳ ጥናት መለየት፤ ደረጃቸውን የጠበቁ መሰረተ-ልማትና ፋሲሊቲዎች የማደረጃት ሥራዎች መሰራታቸው እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡
በማስከተልም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በአቶ ተፈሪ ጊሼ የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ የቀረበ ሲሆን ዕቅዱም የትምህርትና ስልጠና አግባብነት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ማሳደግ፣ የጥናትና ምርምር፣ የማማከር አገልግሎት ማሳደግ፣ የማህበረሰብ ተሳትፎ፣ የሳይንስ ባህል ግንባታ እና የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳደግ፣ የትምህርትና የስልጠና አገልግሎት፣ አሠራርና ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መመሪያዎችና ስታንዳርዶችን ማዘጋጀትና መተግበር፣ የሰው ኃይልና ተቋማዊ አቅምና ብቃት ማጎልበት፣ ቴክኖሎጂ፣ መሠረተ ልማትና ፋሲሊቲ ማሳደግ፣ አጋርነት፣ ትስስር እና አለማቀፋዊነትን ማሳደግ እንዲሁም የበጀት፣ የፋይናንስ፣ የንብረት አስተዳዳር አገልግሎትን ውጤታማነትን ማሻሻልና የውስጥ ገቢ ማሳገድ የሚሉትን ግቦች ያነገበ መሆኑን እና ግቦቹን ለማሳካት የሚከናወኑ ዓላማዎችና ዋና ዋና ተግባራቶችን በዝርዝር በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡
በማስከተልም የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተቀመጡት ስትራቴጂያዊ ግቦችና ዓላማዎች መሰረት የተሰሩ ስራዎችን በሪፖርት ያቀረቡት ሲሆን በትምህርት አገልግሎት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ፤ በጥናትና ምርምር ፤ በስልጠና አገልግሎት ፤ ማማከር አገልግሎት ፤ በማህበረሰብ አገልግሎቶች የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እና የዩኒቨርሲቲው የውስጥ አቅም ግንባት የ2017 ዓ.ም ዋና ዋና የትኩረት መስኮች መሆናቸውን አቶ ተፈሪ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
በግምገማ መድረኩ ላይም የሪፎርም ስራዎች አፈጻጸም ሪፖርት በዶ/ር አብርሃም ሀጎስ የፕሬዚደንት ጽ/ቤት ኃላፊ የቀረበ ሲሆን በሪፖርቱም መሰረት ዩኒቨርሲቲው በየደረጃው የተቀመጡትን መስፈርቶች በማሟላት ሙሉ በሙሉ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በርካታ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸው ተገልጻል፡፡ በዚሁም መሰረት ዩኒቨርሲቲው በ2018 ዓ.ም ከፊል ራስ-ገዝነትን፣ በመቀጠልም በ2019 ዓ.ም ወደ ከፍ ያለ ራስ-ገዝነት ደረጃ በመሸጋገር በመጨረሻም በ2020 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ እራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሆን ፤ ይህ የጊዜ ሰሌዳም በዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድም የጸደቀ መሆኑንና በዚህ የጊዜ ሰሌዳ መሰረትም የሚተገበሩ የሪፎርም ስራዎች ተለይተው በትኩረት እየተሰራባቸው መሆኑን ዶ/ር አብርሃም ገልጸዋል፡፡ በእስካሁኑ ሂደትም ተልዕኮና የትኩረት መስኮችን መለየትና ማጠናከር፣ የራስ-ገዝ የሽግግር ሰነዶችን ማዘጋጀት ፣ የምርምር ምርታማነትና ተጽዕኖ ማሳደግ፣ የውስጥ ገቢን ማሳደግ፣ በቂና ብቁ የሰው ኃይልን ማደራጀት፣ ትብብርና ትስስር ማጠናከር፣ መሰረተ-ልማቶችን ፋሲሊቲዎችን ማደራጀትና የመሳሰሉት ስራዎች በስፋት እየተሰራባቸው መሆኑ ገልጸዋል፡፡
የካውንስሉ አባላትም በቀረበው ዕቅድና የሩብ ዓመት የሥራ የአፈጻጸም ሪፖርት ላይ ያላቸውን አስተያየት እና ግብዐት የሚሆኑ ሀሳቦችን እንዲሁም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባሉ ያሏቸውን ጉዳዮች በማንሳት ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡