19ኛዉ የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በኢሲሰዩ ተከበረ
19ኛዉ የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ “አገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" መሪ ቃል ሕዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዳሴ አዳራሽ ተከበረ፡፡ በዝግጅቱ ላይም የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች፣ መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተለያዩ መሪ ቃላት ሲከበር መቆየቱን አስታውሰው ዘንድሮም በአገራችን ለአስራ ዘጠነኛ ጊዜ “አገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል በፌዴራሊዝም፣ በህገ መንግስት ስርጸትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እየተከበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአገር ግንባታ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት በሚኖረው ሚና ላይ የውይይት ሠነድ አዘጋጅቶ ለትምህርት ተቋማት ማህበረሰብ ተደራሽ በማድረግና ስልጠና በመስጠት፣ ወደስራ የገባ ሲሆን የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲም በስልጠናው ላይ በመሳተፍ በዓሉን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለማክበር ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በመቀጠልም ይህ በመከበር ላይ ያለው 19ኛዉ የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ኢትዮጵያውያን ህብረታቸውን አጉልተው የሚያሳዩበት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታቸው ደምቆ የሚታይበት፣ የጋራ የሆነውን መገለጫቸውን በማድመቅ፣ በመቻቻል እኩልነትን በማስፈን እና አብሮነትን በማስቀጠል ረገድ ውጤት የሚመዘገብበት በዓል መሆኑን የገለጹት ፕ/ር ፍቅሬ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያውን በጋራ ለጋራ ጥቅም እጅ ለእጅ ተያይዘው ሀገራቸውን ወደፊት ለማራመድ ቃል የሚገቡበት እና ህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚገለጽበት፣ በውጤቱም ሀገራዊ መግባባትን የሚረጋገጥበት እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲያችንም የፐብሊክ ሰርቪሱን አቅም የመገንባት ተልዕኮ የተሰጠው እንደመሆኑ የመንግስት አገልግሎቶች ቀልጣፋና ጥራታቸውን የጠበቁ ይሆኑ ዘንድ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ሰራተኞች የፌዴራል ሥርዓቱን ተረድተው ብዝሀነትን ባከበረ መልኩ እና ህዝብን እንዲያገለግሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ ይህን 19ኛዉ የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በዩኒቨርሲቲያችን ስናከብርም በዓሉ በሀገራችን ህዝቦች መካከል አንድነትን በማጉላት፣ ለሀገራዊ መግባባት የሚኖረውን አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ምንም እንኳን በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ ያሉ ቢሆንም ካለፉት ጊዜያት ጀምሮ የነበሩ የሰላም መታጣትና ግጭቶች መኖራቸው ያላጠናቀቅናቸው ሥራዎች መኖራቸውን የሚያሳዩ ናቸው ያሉት ፕ/ር ፍቅሬ የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ በማድረግ ለህዝባችን ሰላም፣ ልማትና አንድነት ሁሉም የባለድርሻ አካላት በአንድነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይም የመወያያ ጽሑፍ በዶ/ር ግሩም ክንፈ ሚካኤል የፌደራሊዝም ትምህርት ክፍል ኃላፊ የቀረበ ሲሆን ዶ/ር ግሩም በጽሁፋቸው በማህበረሰቡ ዘንድ በፌዴራሊዝም እና በፌዴራል ሥርዓት ላይ ወጥ የሆነ ግንዛቤ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ሂደት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ሂደት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች መካከልም የፌዴራል ሥርዓቱ በተገቢው ለመተግበር የሚያስችል ፌዴራላዊ እሳቤ በተገቢው ደረጃ አለመዳበር፣ የፌዴራል ሥርዓቱን ለመገንባት መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በአገሪቱ ልሂቃን መካከል ደረጃውን የጠበቀ መግባባት አለመፈጠር፣ ህገመንግስታዊነት አለመዳበር፣የዲሞክራሲ አለመዳበር፣ የዳበረና ተቋማዊነትን የተላበሰ የመንግስታት ግንኙነት በተገቢው ሁኔታ አለመገንባት፣ሥርዓቱን ለመተግበር አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት እና የአሰራር ሥልቶች አለመዳበር እና የመሳሰሉት ተግዳሮቶችን ለአብነት አሳይተዋል፡፡ ለእነዚህ ተግዳሮቾችም የመፍትሔ አማራጮችን ሲጠቅሱ በፌዴራሊዝምና በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ ትክክለኛ እይታ መገንባት፣ የፌዴራል ሥርዓትን ለመገንባት ሀገራዊ መሰረት በሆኑ ጉዳዮች ላይ መግባባትን መፍጠር፣ ህገ-መንግስታዊነትን ማዳበር፣ በየወቅቱ ለሚነሱ ጉዳዮች ፌዴራላዊ በሆነ አግባብ ምላሽ መስጠት፣ አክራሪ ብሔርተኝነትን በማዳከም ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጎልበት፣ ብዝሀነትን ተቀብሎ በየደረጃው ማስተናገድና ሀገራዊ አንድነትን ማጎልበት እና የመሳሰሉት ጉዳዮችን በመፍትሔነት አቅርበዋል፡፡
በውይይቱ ላይም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳብና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን የግለኝነት መስፋፋት፣ የሀገራዊ ስሜት መዳከም፣ የስልጣን ፍላጎት፣ የማያግባቡ ነገሮች መብዛት እና ሌሎችም ወቅታዊ ጉዮች የሀገር ፈተናዎች መሆናቸውን ተጠቅሰው ካለፈው ስህተት በመማርና ወደ እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል በጥልቀት ወደራሱ በመመልከት እና ለመጪው ትውልድ በማሰብ ሀገራዊ መግባባት ላይ መድረስ ተገቢ መሆኑ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡